ቀጥታ፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ፅዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት እያስቻሉ ነው 

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፡-በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከናወኑ የአካባቢ ጥበቃና የልማት ስራዎች ፅዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት እያስቻሉ መሆኑ ተገለፀ።

የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ በወጡ ሕጎች፣ ደንቦች፣ ማዕቀፎችና አሰራሮች ላይ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት ጀምሯል።


 

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ በወቅቱ እንደገለጹት፤ መንግስት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ያደረጋቸው የልማት ስራዎች ውጤታማ ናቸው። 

በተለይም የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የተከናወኑ ተግባራት ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ትልቅ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የአካባቢ ጥበቃና ልማት ስራዎችን በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል የሚያስችሉ የለውጥ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አንስተዋል። 


 

የአካባቢ ጥበቃ ስራ የመንግስት ወይም የአንድ ተቋም ኃላፊነት አለመሆኑን ያመለከቱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ህብረተሰቡንና የተለያዩ ተቋማትን በማስተባበር ቀጣይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ምርምር ማዕከል ኃላፊ ፕሮፌሰር በላይ ሰማኒ በበኩላቸው፤ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን ከዘላቂ የልማት ግቦች በማቀናጀት ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገልጸዋል። 


 

ስለሆነም የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲዎችንና አዋጆችን በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ ዘላቂ የልማት ዕቅዶችን ለማሳካት በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የተመድ የልማት ፕሮግራም (UNDP) የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ባይድ ዶ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በተለይም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ እንዲሁም የካርበን ልቀትን ለመቀነስ የተከናወኑ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን በተጨባጭ መመልከታቸውን ጠቅሰዋል።

ይህ ስልጠናም በኢትዮጵያ የተጀመሩ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን ከሀገራዊ የልማት ዕቅዶች ጋር አጣጥሞ ለማስኬድ የሚያስችል አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም