ቀጥታ፡

የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የሀገር ሽማግሌዎች ድጋፋቸውን ያጠናክራሉ

ባህር ዳር ፤ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሚደረገው የተቀናጀ ጥረት የሀገር ሽማግሌዎች ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ገለጹ።

"ማህበራዊ ሃብቶቻችን ለዘላቂ ሰላምና ለኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችን" በሚል መሪ ሀሳብ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች የተሳተፉበት የምክክር መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።


 

ከኦሮሚያ ክልል የመጡት አባ ገዳ አብዱራዛቅ አህመድ፤ለዘላቂ ሰላም የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአማራ ክልል ሰላምን ለማጽናት የሀገር ሽማግሌዎች እያደረጉ ያለው ጥረት ውጤት እያመጣ በመሆኑ መጠናከር አለበት ብለዋል።


 

ችግሮች ሲከሰቱ በሰላማዊና በሽምግልና ስርዓት መፍትሄ መስጠት የቆየ የኢትዮጵያዊያን ባህል መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመጡት የጋሞ የሀገር ሽማግሌ አቶ ሰዲቃ ስሜ ናቸው። 


 

የሽማግሌዎች ምክርና ተግሳጽ ለሰላም መጽናት የጎላ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰው፤ የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆነው ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጩ የማድረግ የካበተ ልምድ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ሰላምን ለማጽናት የክልሉ የሀገር ሽማግሌዎች ባደረጉት ጥረት ለውጥ እየታየ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል የሀገር ሽማግሌ አቶ ጫኔ መንገሻ ናቸው።


 

ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ስለሰላም በጋራ መምከር መቻላቸው ለክልሉ የሀገር ሽማግሌዎች ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

የሰላም ሚኒስትሩ መሐመድ እንድሪስ እንደገለጹት፤ ሰላምና አብሮነትን የሚያጠናክሩ ሀገራዊ እሴቶችን አጎልብቶ ለትውልድ ለማስተላለፍ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ሚና የላቀ ነው።


 

ሀገር በትውልድ ቅብብሎሽ እንደምትቀጥል አንስተው፤ ለዚህም ሀገራዊ አንድነትን የሚያፀኑና ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችሉ እሴቶችን ማዳበርና ማጽናት ያስፈልጋል ብለዋል።

የሰላም ማኒስቴር ነባርና የዳበሩ ባህላዊ እሴቶችን ለማልማትና ለማደራጀት በሚደረጉ ጥረቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ለሽምግልና ስርዓት ትኩረት መስጠቱ እንደሚበረታታ ገልጸው፤ በክልሉ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የሀገር ሽማግሌዎች ከመንግስት ጎን በመሆን ባከናወኑት ተግባር ተጨባጭ ውጤት መምጣቱን ገልጸዋል።


 

የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በክልሉ ለተገኘው ሰላም የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ሚና ከፍ ያለ ነው ብለዋል።

ባለፉት ጊዜያት በተቀናጀ መንገድ በተሰራው ሥራ የተገኘውን ሰላም ዘላቂነት በማረጋገጥ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ጥረታቸውን ይበልጥ እንዲያጠናክሩ አስገንዝበዋል። 

በመድረኩ ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የክልሉና የፌደራል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም