በህዝቡና በጸጥታ ሃይሉ ጠንካራ ትብብር ዘላቂ ሰላምና ልማት የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በህዝቡና በጸጥታ ሃይሉ ጠንካራ ትብብር ዘላቂ ሰላምና ልማት የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል
ሰቆጣ ፤ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፡- በህዝቡና በጸጥታ ሃይሉ ጠንካራ ትብብር ዘላቂ ሰላምና ልማት የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን በአማራ ክልል የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ገለጸ።
የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ከሰሃላ ሰየምት ወረዳ ነዋሪዎች ጋር በሰላም ግንባታ ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂዷል።
የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪና የኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሹመት ጥላሁን በወቅቱ እንዳሉት፤ የሰሃላ ወረዳ ህዝብ ለሰላም መፅናት ያበረከተው አስተዋጽኦ በአርአያነቱ የሚጠቀስ ነው።
ህብረተሰቡ ለሰላም ግንባታ ያለው ጽኑ እምነት የጥፋት ቡድኑ አባላት መንግስት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ አድርጓል ብለዋል።
ህብረተሰቡን ከጸጥታ ተቋማት ጋር በማቀናጀት ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል አሰፋ ቸኮል በበኩላቸው፤ የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎችን መቀበሉ እንዳለ ሆኖ ከጥፋት አላማቸው ባልተመለሱት ላይ ህግ የማስከበር እርምጃው ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ሙሉነሽ መኮንን እና አቶ ካባው መንግስቴ፤ የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ ከመንግስት ጋር በመሆን ሌት ከቀን እየሰራን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የብሄረሰብ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።