የባሌ ሮቤ ሪጅን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ደንበኞች የኃይል መቆራረጥ ችግር እንዲፈታላቸው ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
የባሌ ሮቤ ሪጅን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ደንበኞች የኃይል መቆራረጥ ችግር እንዲፈታላቸው ጠየቁ
ሮቤ፤ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል የባሌ ሮቤ ሪጅን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ደንበኞች የኃይል መቆራረጥ ችግር እንዲፈታላቸው ጠየቁ።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የባሌ ሮቤ ሪጅን በበኩሉ የሃይል መቆራረጥ ችግርን በአጭርና የረጅም ጊዜ መፍታት የሚያስችል ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል።
አገልግሎቱ ከባሌ ሮቤ ሪጅን ቁልፍ ደንበኞችና ባለድርሻ አካላት ጋር በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ የተሰማሩ ደንበኞች የኤሌክትሪክ የሀይል መቆራረጥ በስራቸው ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊ ቁልፍ ደንበኞች መካከል አቶ ኡመር አማን፤ በከተማዋ የሚስተዋለው የሃይል መቆራረጥ በዕለት ተዕለት ተግባራቸው ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የባሌ ቅርንጫፍ ተወካይ አቶ አብዳ ሀሰን፤ በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና መዋዥቅ የምርጥ ዘር ማበጠር ስራቸው ላይ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የባሌ ሮቤ ሪጅን ዳይሬክተር አቶ ባሙድ ሁሴን፤ በደንበኞች የተነሱ ችግሮች ትክክል በመሆናቸው ለዘላቂ መፍትሄ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በመሆኑም ችግሩን በአጭርና የረጅም ጊዜ ለመፍታት የሚያስችል ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ስለመሆኑ አስረድተዋል።
በአጭር ጊዜ ለመፍታት በከተማዋ የተጀመረው ንዑስ ማከፋፈያ ጣቢያ በቅርቡ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ተናግረዋል።
የንዑስ ጣቢያው ለአገልግሎት መብቃትም የፈረቃ የኤሌክትሪክ አጠቃቀምን እንደሚያስቀር አክለዋል።
ተቋሙ በአቅርቦትና ፍላጎት ልዩነት የተፈጠረውን ክፍተት በዘላቂነት ለመፍታት ቋሚ ጣቢያ እንደሚገነባም አስረድተዋል።
የኤሌክትሪክ መስመር ጥራትና አሰራሩን ዲጂታላይዝ በማድረግ የሃይል መቆራረጥና ብክነትን ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የባሌ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙክታር ማሚያ፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞችን አገልግሎቶች ለማዘመንና ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀው አስተዳደሩም አስፈላጊውን እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።