ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የስደተኞችን መብትና ደኅንነት በማስከበር ረገድ ያላትን ዓለም አቀፍ ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ የስደተኞችን መብትና ደኅንነት በማስከበር ረገድ ያላትን ዓለም አቀፍ ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ዛሬ በዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን አከባበር ላይ በስደት ዙሪያ በጎ ተጽዕኖ የፈጠሩና ለውጥ ያመጡ አካላትን “የስደት ሻምፒዮን” በሚል ተከብሯል።

በዚህ ወቅት፥ መንግሥት በዜጋ ተኮር ፖሊሲው በተለያዩ ሀገራት በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን በክብር ወደ ቤታቸው የመመለስና የማቋቋም ሥራን ቀዳሚ ትኩረቱ አድርጓል ብለዋል።

እኛ ስደተኞችን የችግር ምንጭ ሳይሆን የሀገራትን ኢኮኖሚ የሚያጠናክሩ እና ማኅበረ ባህላዊ ትሥሥርን የሚያጎለብቱ የፈጠራ፣ የስኬትና የለውጥ ኃይሎች አድርገን እንመለከታቸዋለን ነው ያሉት።


 

ኢትዮጵያ በመደመር ዕሳቤዋ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ከ1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞን ተቀብላ ታስተናገዳለች ያሉት አቶ ተመስገን፥ ተገቢውን ከለላና ድጋፍ በመስጠት በዓለም አቀፉ የስደተኞች ስምምነት ትግበራ ላይ ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተወጣች ነው ብለዋል።

ለስደተኞች መብትና ክብር መቆም የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የሁላችንም የሞራል ግዴታ መሆኑን መገንዘብ ይገባል።ስደት ሕጋዊ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ሰብአዊነትን ያከበረ እንዲሆን ዓለም አቀፋዊ ቅንጅትን ማጠናከር ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያ የስደተኞች መነሻ፣ መሻገሪያ እና መድረሻ እንደመሆኗ ለሁሉም አካታች እና ሰብአዊ ዓለም ለመገንባት ያላትን ቁርጠኝነት አጠናክራ እንደምትቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም