ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ ዲጂታል ግብርናን የማስፋት አካል የሆነ የግብርና ትምህርት መስጫ ሥርዓት ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 9/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዲጂታል ግብርናን ለማስፋት የጀመራቸውን ተግባራት የሚያጠናክር አግሪለርን(AgriLearn) የተሰኘ ዲጂታል የግብርና ትምህርት መስጫ ሥርዓት ይፋ አደረገ።

ዲጂታል የትምህርት መስጫ ስርዓቱ በግብርናው ዘርፍ ለሚሰማሩ ወጣቶች በዲጂታል መንገድ ግብርናን በተመለከተ የተሟላ ትምህርት የሚያገኙበት ነው ተብሏል፡፡

የመተግበሪያው ዋና ዓላማ ዘመናዊ የግብርና አሠራሮችን፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምንና ምርጥ ተሞክሮዎችን በዲጂታል መንገድ ማድረስ ሲሆን ይህም ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚረዳ ተጠቅሷል፡፡


 

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ አግሪለርን የኢንተርኔት ግንኙነት ባለበት በማንኛውም ቦታ ሆኖ ትምህርቶችን መከታተል የሚያስችል ነው፡፡

AgriLearn ኢትዮጵያ ዲጂታል ግብርናን ለማስፋት የያዘችው ትልቅ ስትራቴጂ አካል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ወጣቶችን በግብርና ስራ ፈጠራ ለመሰማራት ክህሎትና በራስ መተማመን እንዲኖራቸው የሚያደርግ ሲሆን የበለፀገችና ጠንካራ ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደትም አጋዥ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ይበልጥ ለማፋጠን ዘመናዊ የዲጂታል ትምህርት መድረክ መሆኑን ገልጸው፥ ወጣቶች ሙሉ የስልጠናውን ትምህርት ሲያጠናቅቁ የምስክር ወረቀት በኦንላይን የሚያገኙበት ሥርዓት እንዳለው አንስተዋል።

ወጣቶች ስለግብርና ቴክኖሎጂዎች፣ ስለግብዓት አጠቃቀም በቂ እውቀት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ብለዋል።


 

በኢንስቲትዩቱ የአደይ ፕሮግራም ዳይሬክተር ኃይሌ ዴሬሳ፤ ዲጂታል የትምህርት ሥርዓቱ አሁን ላይ አምስት የትምህርት ዓይነቶችን በውስጡ የያዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአቮካዶ፣ የበቆሎ፣ የሽንኩርት ዘር ማምረት፣ የእንቁላል ዶሮ እና የንብ ማነብ ስራዎችን እንዴት ማከናወን እንደሚቻልና የሚያስፈልጋቸውን ግብዓቶች ያካተተ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ 41 የምርት ዓይነቶችና የአመራረት ዘዴዎችን ለማካተት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው የግብርና ቢዝነስ ላይ ለሚሰማሩ ዜጎች ወሣኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም