ቀጥታ፡

ሰላማዊ አማራጮችን ተከትሎ ችግሮችን መፍታት ለአካታች ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት የላቀ ሚና አለው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 9/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሰላማዊ አማራጮችን ተከትሎ ችግሮችን መፍታት ለአካታች ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት የላቀ ሚና እንዳለው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) ገለጹ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር)፤ እንደ ሀገር የማያግባቡ ጉዳዮችን በመለየት መምከርና ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ ማስቀመጥ የኮሚሽኑ ዓቢይ ተልዕኮ ነው ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ በምክክሩ ማንኛውንም በሰላማዊ መንገድ ለመወያየት ፍላጎት ያላቸውን አካላት ለማሳተፍና ሃሳባቸውን ለማካተት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ባለፉት ዓመታት ከመንግስት፣ ከሐይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ባከናወናቸው ተግባራት በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል፡፡

የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ አማራጭ መመለስ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት መሰረት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን መምረጣቸው ለምክክር ሂደቱ ትልቅ አዎንታዊ እርምጃ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ምክክሩን ይበልጥ አካታች እንደሚያደርገውና ለስኬቱም ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ እየታዩ ያሉ የሰላም አማራጮች እንደ ሀገር ለሚጠበቀው እድገት ትልቅ መሰረት ይዘው መምጣታቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም