ቀጥታ፡

ሕንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ትብብር በይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ታኅሣስ 9/2018 (ኢዜአ)፡- ሕንድ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር የምታከናውናቸው ተግባራት በይበልጥ ተጠናክረውና ሰፍተው እንደሚቀጥሉ የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ራንዲር ጃይስዋል ተናገሩ።

የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ላለፉት ሁለት ቀናት በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወቃል።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ራንዲር ጃይስዋል ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ (ፒኦኤ) ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸውም ኢትዮጵያ እና ሕንድ በታሪክም በባህልም የሚጋሯቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ እና የሚያመሳስሏቸው ብዙ ነገሮች መኖራቸውን አንስተዋል።

ለአብነትም ሀገራቱ የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ እና ሕንድ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ የሕዝብ ለሕዝብና የባሕል ትሥሥር ያላቸው ሀገራት መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በመሆኑም ግንኙነታቸው እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ የሀገራቱ ግቦች በደቡብ ደቡብ ትብብር ላይም ዕሳቤዎቻቸው ተጣጥመው እና በይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።

ይህም ኢትዮጵያና ሕንድ በዓለም አቀፍ መድረኮች የታዳጊ ሀገራትን ድምጽ ለማሰማት በትብብር እንዲሠሩ ይጠቅማል ነው ያሉት።

በርካታ ዓመታትን የዘለቀው የሀገራቱ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት ወደ ስልታዊ ግንኙነት ማደጉም ያላቸውን ጠንካራ ወዳጅነት ያሳያል ብለዋል።

ሕንድ ከአፍሪካ ጋር ለሚኖራት ግንኙነት አዲስ አበባ ማዕከል መሆኗን የጠቆሙት ቃል አቀባዩ፤ ሀገራቸው ከአፍሪካ ኅብረት ጋርም በትብብር እንደምትሠራ ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ወዳጅነትና አጋርነት ለሕንድ በጣም አስፈላጊ እና ተገቢ መሆኑንም በአጽንኦት ገልጸው፤ በተለያዩ ዘርፎች ያሉ ትብብሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም