ቀጥታ፡

የግብርና ፋይናንስ ተደራሽነት ምርታማነትን ለማሳደግ ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፡-የግብርና ፋይናንስ ተደራሽነት የገጠር ትራንስፎርሜሽን ለማሳካት እና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ወሳኝ በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግብርናን በዘላቂነት ለመደገፍና የገጠር ኢኮኖሚ እድገትን ለማጎልበት ለአርሶና አርብቶ አደሮች የግብርና ብድር አገልግሎት በይፋ አስጀምሯል።


 

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የግብርና ፋይናንስ በማሳደግ የገጠር ትራንስፎርሜሽን አጀንዳን በማሳካት ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

ዛሬ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  ይፋ ያደረገው የብድር አገልግሎት አካታች የሆነ የፋይናንስ ተደራሽነትን በገጠር ለማረጋገጥ አንዱ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ባንኩ ለአርሶ አደሩና ለአርብቶ አደሩ የጀመረው አገልግሎት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑንም አመልክተዋል።


 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  የኮርፖሬት አገልግሎቶች ምክትል ፕሬዝዳንት ኤፍሬም መኩሪያ፤ የብድር አገልግሎቱ የአነስተኛ ባለ-ይዞታ አርሶና አርብቶ አደሮችን የብድር ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

አገልግሎቱ አርሶ አደሮች በግለሰብ ደረጃም ሆነ ተደራጅተው ከግብርና ግብዓቶች እስከ  ማሽነሪዎች ግዥ  ለመፈጸም ብድር የሚያገኙበት መሆኑን ገልጸዋል።


 

አርብቶ አደሮች ለእንስሳት ምርታማነት የሚያስፈልጓቸውን ግብዓቶች ለማሟላት የብድር አገልግሎቱ ትልቅ ዕድል መፍጠሩንም ተናግረዋል።

አርሶ አደር ሽመልስ ገመቹ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም በራሳቸው ካፒታል ይንቀሳቀሱ እንደነበር አስታውሰዋል።


 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ በይፋ ያስጀመረው የብድር አገልግሎት የግብርና ስራቸውን ከዚህ በበለጠ አስፍቶ ለመስራት እድል እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ቅርንጫፍ በመሄድ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም