ቀጥታ፡

የበደልነውን ህዝብ በልማት ለመካስ በትጋት እየሰራን ነው 

ሰቆጣ ፤ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፡- ከጥፋት መንገድ ወጥተው የበደሉትን ህዝብ በልማት ለመካስ በትጋት እየሰሩ መሆናቸውን በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በደሃና ወረዳ የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ገለፁ።

በብሄረሰብ አስተዳደሩ በደሃና ወረዳ ቢውል ቀበሌ የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ከመጡ ወጣቶች መካከል ወጣት እምወደው ማሞ ለኢዜአ እንደገለፀው፤ቀደምሲል በተሳሳተ መንገድ ከጥፋት  ቡድኑ ጋር  በመቀላቀል  በህዝብ ላይ በደል ሲያደርስ  ቆይቷል።


 

አሁን ላይ  የስህተት መንገዱን በመረዳት  መንግስት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ በመቀበል ህብረተሰቡን በልማት ለመካስ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።

የተሃድሶ ስልጠና ወስዶ  መንግስት ባደረገለት የመቋቋሚያ ገንዘብ በከብት  ማድለብ ስራ ላይ ተሰማርቶ ራሱን ለመለወጥ እየተጋ እንደሚገኝ ገልጿል።

የጥፋት መንገድን በመተው  ወደ ልማት  መምጣቱ  ህይወቱን ማሻሻል መቻሉን ያነሳው  ወጣቱ ሌሎችም  የጥፋት መንገዱን በመተው  የሰላም ጥሪውን እንዲቀበሉ መክሯል።

መንግስት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ በመቀበል ራሱን በስራ ለመለወጥ እየተጋ መሆኑን የገለጸው ደግሞ  የአምደወርቅ ከተማ ነዋሪ ወጣት ግዛቸው ተፈራ ነው።


 

ከጥፋት ድርጊቱ ተመልሶ የተሀድሶ ስልጠናውን በመውሰድ በመንግስት በተደረገለት የመቋቋሚያ ገንዘብ ድጋፍ የኤሌክትሮኒክስ ጥገናና መሸጫ ሱቅ ከፍቶ እየሰራ እንደሚገኝም ተናግሯል።

የብሄረሰብ አስተዳደሩ የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ሃላፊ ሃምሳ አለቃ አዘዘው አዳነ እንዳሉት፤ በብሄረሰብ አስተዳደሩ ከ500 በላይ የጥፋት ቡድኑን  ተቀላቅለው የነበሩ ዜጎች የሰላም ጥሪ ተቀብለው ገብተዋል።


 

ከዚህ ውስጥም 198 ያህሉ በመንግስት የተሃድሶ ስልጠና ወስደው በተደረገላቸው የመቋቋሚያ ገንዘብ በተለያዩ የስራ ዘርፎች መሰማራታቸውን ጠቁመው ሌሎቹንም ለማቋቋም እየተሰራ ነው ብለዋል።

ሌሎች ጫካ ያሉ የጥፋት ቡድኑ አባላትም የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ህዝባቸውን በልማት ሊክሱ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም