ቀጥታ፡

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ለሥርዓተ ፆታ እኩልነት ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፡-የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ለሥርዓተ ፆታ እኩልነትና ለሴቶች ተጠቃሚነት መረጋገጥ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የክልሎች የሴቶች አደረጃጀት የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።

ኢትዮጵያ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከጀመረቻቸው ስራዎች መካከል የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ አንዱ ነው፡፡

በዚህም የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎትን ለሴቶች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ሀገር አቀፍ የንቅናቄና የግንዛቤ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል።

በመድረኩ ላይ የተገኙ የክልል ሴት አመራሮቹ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ለሥርዓተ ፆታ እኩልነት መረጋገጥ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል። 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ እቴነሽ በየነ፤ ዲጂታል መታወቂያ ለሴቶች የሚያስገኘውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በመረዳት በክልሉ የሚኖሩ ሴቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራን ነው ብለዋል። 


 

በተለይም በገጠር የሚኖሩ ሴቶች ስለ ዲጂታል መታወቂያ ያላቸው ግንዛቤ እንዲያድግ የንቅናቄ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

ዲጂታል መታወቂያ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ በመሆኑ እንደሃገር የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

 የኦሮሚያ ክልል የሴቶች ፌዴሬሽን ዋና ፀሃፊ መርያማ ቡንቲ በበኩላቸው፤ የፋይዳ መታወቂያ በተለይም የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ጠቅሰዋል።


 

ቀደም ባሉ ጊዜያት በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች የመሬት ይዞታ ባለቤትነት መብታቸውን ማረጋገጥ የማይችሉበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰው ፋይዳ ይህንን ችግር መቅረፍ መቻሉን ጠቁመዋል።

የአፋር ክልል ሴቶችና ህፃናት ምክትል ቢሮ ሃላፊ ነስሮ ኡዳ፤ በክልሉ ሴቶችን የፋይዳ መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።


 

ሴቶች የማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ  የፋይዳ መታወቂያ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።  

የሐረሪ ክልል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ምክትል ቢሮ ሃላፊ መፍቱሃ አሊዬ ፤መንግስት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የጀመራቸውን ስራዎች ለማሳካት ሴቶች ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል።


 

ሴቶች የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተከትሎ ከፋይናንስ ተቋማት ብድር በመውሰድ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ማጎልበት የሚችሉበት እድል እንደተፈጠረላቸው አንስተዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም