ግብር ከፋዮች በታማኝነት ግብር በመክፈል የልማት ሥራዎችን ሊያጠናክሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ግብር ከፋዮች በታማኝነት ግብር በመክፈል የልማት ሥራዎችን ሊያጠናክሩ ይገባል
አርባ ምንጭ፤ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በታማኝነት በመክፈል የልማት ሥራዎችን ማጠናከር እንዳለባቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
"ግብር ለሀገር ክብር" በሚል መሪ ሃሳብ ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች የእውቅናና የሽልማት መርሃ- ግብር ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት፤ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በታማኝነትና በወቅቱ በመክፈል ልማትን ማጠናከር አለባቸው ።
ግብራቸውን በታማኝነትና በወቅቱ በመክፈል ሃላፊነታቸውን ለተወጡ ግብር ከፋዮች ዛሬ ምስጋና መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የግብር አሰባሰቡን ውጤታማነት ለማረጋገጥ እንደ ክልል በተከናወነው ተግባር የጌዴኦ ዞን እና ዲላ ከተማ አስተዳደር ግብርን በተሻለ በመሰብሰብ ግንባር ቀደም መሆናቸውንም አቶ ጥላሁን ተናግረዋል።
በቀጣይ ሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች በግብር አሰባሰብ ግንባር ቀደም ለመሆን ጠንክረው እንዲሰሩም አሳስበዋል።
ታማኝ ግብር ከፋዮችም በየአካባቢያቸው በማህበራዊ አገልግሎቶች በመሳተፍ አቅመ ደካሞችን እንዲያግዙ ጠይቀዋል።
እንደ አቶ ጥላሁን ገለጻ፤ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ ለመሰብሰብ በሚደረገው ጥረት አመራሩ ግንባር ቀደም የመሪነት ሚናውን ሊወጣ ይገባል።
በክልሉ የታክስ ስርአትን ለማዘመን የተጀመሩ የዲጂታል ሥራዎችን በሁሉም አካባቢ ለማጠናከር እንደሚሰራም አመልክተዋል።
በግብር ዙሪያ ያሉ ህጎችና አዋጆችን በተመለከተ ግንዛቤ በመፍጠር ገቢን በአግባቡ ለመሰብሰብ በቅንጅት እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ዓለምነሽ ደመቀ፤በበጀት ዓመቱ ባለፉት 5 ወራት ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል።
በክልሉ የዛሬ ተሸላሚዎችን ጨምሮ በርካታ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በታማኝነት በመክፈል የህዝቡ የልማት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
በአንጻሩ የታክስ ህግንና የአሠራር ስርአቱን በመጣስ በግብር ስወራና ማጭበርበር የተሰማሩ ግብር ከፋዮች መኖራቸውን የገለጹት ሃላፊዋ፣ እነዚህን በመከታተል ወደህግ ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም ከ167 የንግድ ድርጅቶች የቀረቡ 1ሺህ 450 ሀሰተኛ ደረሰኞች ለታክስ ዓላማ እንዳይውሉ በማድረግ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ለማዳን ተችሏል ብለዋል።
የገቢ አሰባሰብ ስርአቱን ለማዘመን በተደረገ ጥረት በክልሉ 64 የታክስ ማዕከላት ሙሉ በሙሉ በዲጂታል የታገዘ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በክልሉ ከሚገኙ ታማኝ ግብር ከፋዮች መካከል ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ግብር በመክፈል አንደኛ ተሸላሚ የሆኑት የዲላ ከተማ ዱቄት ፋብሪካ ባለቤት አቶ የሱፍ ጠሃ፤ ግብር የሀገር ልማት እንዲረጋገጥ የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።
ግብርን በታማኝነት መክፈል ያስከብራል ያሉት አስተያየት ሰጪው ያለ ምንም የህግ ተጠያቂነት ስራን በአግባቡ ለመስራትም ፋይዳው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።
ዛሬ የተሰጣቸው ሽልማትና እውቅና ይበልጥ ታማኝ ሆነው እንዲሠሩ ያነሳሳቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በመድረኩ የክልሉ፣ የጋሞ ዞን እና የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።