የከተማዋን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ ልማትን በውጤታማነት ለመፈጸም ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የከተማዋን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ ልማትን በውጤታማነት ለመፈጸም ትኩረት ተሰጥቷል
ባህር ዳር ፤ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፡-በባህር ዳር ከተማ ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ የልማት ፕሮጀክቶችን በውጤታማነት ለመፈፀም እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው ገለፁ።
የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የአምስት ወራት የገቢ ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ዛሬ አካሂዷል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ የከተማዋን ብልፅግና ለማረጋገጥ ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ ይገባል።
የገቢ አሰባሰብ መጠናከር በከተማዋ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅና የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም በበጀት ዓመቱ በዕቅድ የተያዘውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ ልማትን ለማስቀጠል አመራሩ በርብርብ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የአስተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም እሸቴ በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ ከመደበኛና ከማዘጋጃዊ አገልግሎት ገቢ 10 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ባለፉት አምስት ወራት ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል።
የገቢ አሰባሰብ ሂደቱን ዲጂታላይዝድ በማድረግ የደረጃ ‘‘ሀ’’ ግብር ከፋዮች መቶ በመቶ እንዲሁም የደረጃ ‘‘ለ’’ ግብር ከፋዮች ደግሞ 90 በመቶ ግብራቸውን ከወረቀት ንክኪ ነፃ በሆነ መንገድ መክፈላቸውን አስረድተዋል።
በቀጣይም ውዝፍ ገቢን በመሰብሰብ፣ የታክስ መሰረቱን በማስፋትና የክትትልና ቁጥጥር ተግባርን በማጠናከር ለመሰብሰብ በዕቅድ የተያዘውን ለማሳካት ቅንጅታዊ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
የከተማው ልማት ሊፋጠን የሚችለው ገቢን በወቅቱ አሟጦ መሰብሰብ ስንችል ነው ያሉት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊና የፋሲል ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ገረመው አባተ ናቸው።
የግብር ከፋዮችን ግንዛቤ በማሳደግ የታማኝ ግብር ከፋዮች ቁጥር ለማብዛት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የግሽ ዓባይ ክፍለከተማ ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ አስማማው በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የንግዱ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ እንዲከፍልና ህገ ወጦችም ወደ ህጋዊ የንግድ መረቡ እንዲገቡ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
ለግማሽ ቀን በተካሄደው የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ላይ የከተማ አስተዳደሩ፣ የክፍለ ከተማ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።