ቀጥታ፡

የፌደራል ተቋማት ዋነኛ ተልዕኮ የመደመር መንግሥትን እሳቤ በተቋማቸው ተግባራዊ ማድረግ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 9/2018(ኢዜአ)፦ የፌደራል ተቋማት ዋነኛ ተልዕኮ የመደመር መንግሥትን እሳቤ በተቋማቸው ተግባራዊ ማድረግ ነው ሲሉ ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) ገለጹ።

ለፌዴራል ብልፅግና አደረጃጀት አመራሮች ውስጠ ፓርቲ ስርዓት ለማጠናከር ያለመ ስልጠና ተሰጥቷል።


 

በስልጠናው ላይ የፌዴራል ተቋማት ብልፅግና አመራሮች፤ የክላስተሮችና ወረዳ አመራሮች፤ በየደረጃው የሚገኙ የፌዴራል ተቋማት የኢንስፔክሽንና ሥነ-ምግባር አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የፌዴራል ተቋማት አደረጃጀት ፖለቲካ ዘርፍ ሰብሳቢ ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) የፌደራል ተቋማት ዋነኛ ተልዕኮ የመደመር መንግሥትን እሳቤ በተቋማቸው ተግባራዊ ማድረግ መሆኑን በስልጠናው አንስተዋል።

ይህንን ተልዕኳቸውን ከግብ እንዲያደርሱ በፓርቲው ሁለተኛ ጉባኤ ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን መሰረት በማድረግ አደረጃጀቶችን ማጠናከር፣ ተቋማዊ አሰራርን መዘርጋት፣ ጠንካራ የአመራርና አባላት አመለካከትና ስነምግባር መፍጠር ዙሪያ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል።

በፌዴራል ተቋማት አደረጃጀት በዋናነት የጉባኤ አቅጣጫዎችንና የሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማና የሱፐርቪዥን ግኝቶችን መነሻ በማድረግ የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።


 

ዶክተር ተስፋዬ በልጅጌ ጨምረው እንደተናገሩት የተለዩ ክፍተቶችን በስልጠና መሙላት አንዱ ግብ ነው።

በዛሬው ዕለት ለከፍተኛ አመራሮች የተሰጠው ስልጠና ማለም፣ ማቀድና መፈፀም የሚችል አመራር መፍጠር የሚያስችል እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ወስጠ ፓርቲ ስርዓትን በመገንዘብ ተልዕኮን በውጤታማነት ለመፈጸም እንደሚያግዝም ነው ያስገነዘቡት።

በ2018 ዓ.ም ዕቅዶች ውስጥ የፖለቲካና የአደረጃጀት ስራዎችን በማካተት እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመው ቀጣይ ትኩረት የሚጠይቁ ጉዳዮች ተለይተው እየተሰራባቸው ይገኛልም ነው ያሉት።

በፓርቲው ውስጠ አሰራር ላይ ትኩረት ያደረጉ የስልጠና ሰነዶች፥ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የብልፅግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ካሊድ አልዋን እና በኢንስፔክሽንና ስነምግባር ኮሚሽን ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሀብታሙ ሲሳይ ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸውም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም