ቀጥታ፡

በደረቅ ቆሻሻ መልሶ መጠቀም ላይ የተሰማሩ ማህበራት ለከተማዋ ጽዳት መጠበቅ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፡-በአዲስ አበባ በደረቅ ቆሻሻ መልሶ መጠቀም ላይ የተሰማሩ ማህበራት ለከተማዋ ጽዳት መጠበቅ የድርሻቸውን በመወጣት ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ።

የምግብ ማሸግያዎች፣ የዕቃ መጠቅለያዎች፣ ቁርጥራጭ ወረቀቶች፣ የውሃ ማሸጊያ ፕላስቲኮች፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችና በአጠቃላይ አገልግሎት ሰጥተው ያበቁ አልባሳትን ጨምሮ ሌሎች ቁሳቁሶች በደረቅ ቆሻሻ ውስጥ ይመደባሉ፡፡ 

እነኚህ ቁሳቁሶች በአግባቡ ካልተወገዱ አካባቢን በመበከል በሰውም ሆነ በእንስሳት ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ 


 

በአግባቡ ከተከማቹና ከተያዙ ደግሞ መልሰው ጥቅም ላይ ሊውሉ ከመቻላቸውም በላይ ሀብት ሆነው ለሌሎች ወገኖች የስራ ዕድል መፍጠር ያስችላሉ፡፡ 

በመዲናዋ ኢዜአ ያነጋገራቸውና በዘርፉ የተሰማሩ ማህበራት የፕላስቲክ ውጤቶችና የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን መልሶ በመጠቀም የተሻለ ገቢ ከማግኘት ባለፈ ጽዱና ንጹህ አካባቢ ለመፍጠር  የድርሻችንን በመወጣት ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡ 

የኢኬቲ ንግድና ኢንቨስትመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል መኮንን፤ የፕላስቲክ ውጤቶች ቶሎ ስለማይበሰብሱ ለአካባቢ ብክለት ዋነኛ መንስኤ ናቸው ብለዋል፡፡ 


 

ድርጅታቸው የፕላስቲክ ውጤቶችን መልሶ በመጠቀም ለቤት ውስጥ መገልገያና ለተለያዩ ዕቃዎች ማሸጊያ እንዲውሉ በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል ።

በዚህም የአካባቢ ብክለትን በመቀነስ ንጹህ አካባቢ ከመፍጠር ባለፈ አራት መቶ ለሚሆኑ  ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ 

የሄፊሊ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች መልሶ መጠቀም ድርጅት ማናጀር አቶ ቴዎድሮስ ካሳው፤ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች በአግባቡ ካልተወገዱ ለሰውና ለእንስሳት  ጤና ስጋት መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

ድርጅታቸው ከተበላሹ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ብረት፣ አልሙኒዬምና መዳብ በማውጣት መልሰው አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ዴሲሳ ፤ከተማዋን ስማርት ሲቲ ለማድረግ የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች፣ መዝናኛ ፓርኮችና አረንጓዴ አካባቢዎች በስፋት መገንባታቸውን ተናግረዋል፡፡


 

ኤጀንሲው የመሰረተ ልማቶቹን ዘላቂነት ለማረጋገጥ በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡ 

በዚህም በደረቅ ቆሻሻ መልሶ መጠቀም ላይ የተሰማሩ ማህበራት ለከተማዋ ጽዳት መጠበቅ ከፍተኛ ድርሻ መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡


 

በ2017 በጀት ዓመት በመልሶ መጠቀም የተሰማሩ ማህበራት  ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ  ዓመትም  515 ሚሊየን ብር ገቢ  እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡

ኤጀንሲው በዘርፉ ለተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች የገበያ ትስስር በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም