በጎርጎቻ ተራራ ላይ በተሰራ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የተፈጥሮ ሀብቱን መታደግ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በጎርጎቻ ተራራ ላይ በተሰራ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የተፈጥሮ ሀብቱን መታደግ ተችሏል
ጂንካ፤ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፡- በአሪ ዞን ባለፉት ሶስት ዓመታት ጎርጎቻ ተራራ ላይ በተሰራ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የተፈጥሮ ሀብቱን ከመጥፋት መታደግ እንደቻሉ የባካዳውላ አሪ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ።
የጎርጎቻ ተራራ በጂንካ ከተማ እና በባካዳውላ አሪ ወረዳ አዋሳኝ የሚገኝ ተራራ ነው።
ተራራው ከዚህ ቀደም ትኩረት ባለማግኘቱ ምክንያት የመራቆት አደጋ አጋጥሞት እንደነበር የአከባቢው አርሶ አደር ወንድይፍራው ፈለቀ ያስታውሳሉ።
በተራራው ላይ ያለው ደን በመመናመኑ በአከባቢው በተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋ ይከሰት እንደነበር ጠቁመው አልፎ አልፎ በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት እንደሚያጋጥም ተናግረዋል።
የእርሻ ማሳቸውም በጎርፍ በመታጠቡ ለምነቱን ማጣቱን እና ምርት መስጠት አለመቻሉን ጠቁመው ባለፉት ሶስት አመታት በተራራው ላይ በተጀመረው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ተራራውንና የተፈጥሮ ሀብቱን መታደግ መቻሉን ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም ለተለያዩ አገልግሎት ሲጠቀሙበት የነበረ ምንጭ የመድረቅ አደጋ አጋጥሞት እንደነበረ ያስታወሱት አርሶ አደሩ ተራራው መልማት ከጀመረ ወዲህ የውሃ ምንጮች መጠናቸው እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ አርሶ አደር ካሳ ሰኒ በበኩላቸው የጎርጎቻ ተራራ ለመድሃኒትነት የሚውሉ በርካታ ዕፅዋት እንዳለው ጠቁመው ከደኑ የሚወጣው ንፁህ አየርም የመንፈስ እርካታን የሚሰጥ ነው ብለዋል።
"ባለማወቅ ከዚህ ቀደም የተፈጥሮ ሀብቱን ያለ አግባብ ስንጨፈጭፍ ነበር" ያሉት አርሶ አደሩ በአሁኑ ሰዓት ተራራው የቀድሞ ግርማ ሞጎሱን እየተላበሰ መምጣቱንና ተራራው በመልማቱ የጎርፍ አደጋን መከላከል እንዳስቻለ ተናግረዋል።
በአሪ ዞን ግብርና መመምሪያ የተፋሰስ ልማት ባለሙያ መንግሥቱ አስፋው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የተራቆቱ አከባቢዎች እንዲያገግሙ በማድረግ ተስማሚ ስነ-ምህዳር እንዲፈጠር አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዞኑ የጎርጎቻ ተራራን ጨምሮ በየአካባቢው ያለውን ተፋሰስ ለማልማት ወደ ተግባር መገባቱንና በዚህም ተጨባጭ ለውጦች መምጣታቸውን ገልጸዋል።
ባለፈው አመት በዞኑ በ21 ሺህ 986 ሄክታር መሬት 105 ንዑስ ተፋሰሶች መልማታቸውን ጠቁመው 212 ሺህ የሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች በልማቱ መሳተፋቸውንም ጠቁመዋል።
በዘንድሮ አመትም ከታህሳስ መጨረሻ ጀምሮ የተፋሰስ ልማት ንቅናቄ ለማድረግ የሚያስችሉ የቦታ መረጣና አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በዘንድሮ የተፋሰስ ንቅናቄም በዞኑ 24 ሺህ 97 ሄክታር መሬት ላይ 106 ንዑስ ተፋሰሶች የሚለሙ ሲሆን 131 ሺህ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለማሳተፍ ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል።