የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የስራዎቻቸው ማዕከል ሊያደርጉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የስራዎቻቸው ማዕከል ሊያደርጉ ይገባል
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፡-የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የስራዎቻቸው ማዕከል ሊያደርጉ እንደሚገባ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በተዘጋጁ የጥበባት እና ፈጠራ ኢንዱስትሪ ረቂቅ ፖሊሲ፣ ሌሎች የህግ ማዕቀፎች እና በጸደቁ የአሰራር መመሪያዎች ላይ ከሚመለከታቸው የዘርፉ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር ሲያካሂድ የቆየው ውይይት ተጠናቋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ለኢዜአ እንደገለጹት የኪነ ጥበብ ሥራዎች የሀገርን ገጽታ ለመገንባት እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅምን እና አቋምን ለማንጸባረቅ ከፍተኛ ሚና አላቸው።
መንግሥት ከየትኛውም ጊዜ በላይ ለዘርፉ ትኩረት መስጠቱን ገልጸው፥ ኪነ ጥበብን በስርዓተ ትምህርት ከማካተት አንስቶ በሚከናወኑ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችም ላይ መንፀባረቁን በማሳያነት አንስተዋል።
ይህንን በመጠቀም ለሕዝብ እና ለሀገር መስራት ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የስራዎቻቸው ሁሉ ማዕከል ሊያደርጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በዘርፉ ያለውን አቅም አጉልቶ ለማውጣት በተቀናጀ አግባብ መስራት እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
በሁሉም መስክ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ ያላቸውን አይተኬ ሚና እንዲጫወቱ ቀጣይነት ያላቸው ስራዎች እንደሚከናወኑ ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።