ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጸኑ ሀገራዊ እሴቶችን ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል - ሚኒስትር መሐመድ እንድሪስ - ኢዜአ አማርኛ
ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጸኑ ሀገራዊ እሴቶችን ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል - ሚኒስትር መሐመድ እንድሪስ
ባህር ዳር፤ ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፦ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጸኑ ሀገራዊ እሴቶችን ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትር አቶ መሐመድ እንድሪስ ገለጹ።
በባህር ዳር ከተማ "ማህበራዊ ሀብቶቻችን ለዘላቂ ሰላምና ለኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችን" በሚል መሪ ሃሳብ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት መድረክ እየተካሄደ ነው።
የሰላም ሚኒስትሩ መሐመድ እንድሪስ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ኢትዮጵያ አብሮነትን የሚያጎለብቱና ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚያስችሉ የዳበሩ ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ናት።
እነዚህን ሀገራዊ አሴቶችን በመጠበቅና በማዳበር ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ መስራት እንደሚገባ ገልጸው ለዚህም የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ድርሻ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
"ሀገር በእድገት ጎዳና ጸንታ የምትዘልቀው በትውልድ ቅብብሎሽ ነው" ያሉት ሚኒስትሩ ለዚህም ባህላዊ እሴቶችን ይበልጥ ማሳደግ ላይ ትኩረት መስጠት ይገባል ብለዋል።
የሰላም ሚኒስቴር ነባር ባህላዊ የግጭት መፍቻ እሴቶችን ለማልማትና ለማደራጀት በሚከናወኑ ተግባራት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
መንግስት ግጭቶች በምክክር እንዲፈቱ ትናንትም ዛሬም እየሰራና ለሰላምም እጁን ዘርግቶ ይገኛል ሲሉም አክለዋል።
ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ የዛሬው መድረክም የህብረተሰቡ የሽምግልና እሴቶች ለሰላም ግንባታ ያላቸውን ሚና ለማጎልበት ያለመ ነው ብለዋል።
"የክልሉ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ተባብሮና ተከባብሮ የመኖር የዳበረ እሴት ያለው ነው" ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ ናቸው።
የክልሉ መንግስት ለሽምግልና ስርዓት መጎልበት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በክልሉ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የክልሉ ህዝብ ሰላምን አጥብቆ ከመሻት ባለፈ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት የዳበረ እሴት ያለው ቢሆንም በውስጥ ባንዳዎችና በውጭ ባዳዎች ጥምረት የግጭት ማዕከል እንዲሆን መደረጉን ገልጸዋል።
መንግስት ግጭቱ በሰላም እንዲቋጭ የሰላም እጁን መዘርጋቱን ገልጸው እስካሁን በተደረገው ጥረት የታጠቁ ሃይሎች የሰላም አማራጩን ተቀብለው መምጣታቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ እስካሁን ለመጣው ለውጥ የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ የክልሉ መንግስት ለሽምግልና ስርዓት መዳበር አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
በምክክር መድረኩ ላይም የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ ሥራ ሃላፊዎች፣ ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።