በክልሉ የፍትህ አገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ይበልጥ ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የፍትህ አገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ይበልጥ ሊጠናከር ይገባል
አዳማ ፤ ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የፍትህ አገልግሎት ጥራትና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባ የፍትህ አካላት ገለጹ።
የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና ሃዳ ሲንቄዎች በፈትህ ስርአቱ ውስጥ የሚኖራቸውን እገዛ ማጠናከርን ያለመ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የምስራቅ ኦሮሚያ ምድብ ቋሚ ችሎት አስተባባሪ ረታ በቀለ፤ የፍትህ ስርአቱን ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህ ሂደት የመንግስትና ባለደርሻ አካላት ጥረት እንዳለ ሆኖ በተለየም የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና ሃዳ ሲንቄዎች ሚና የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የፍትህ አገልግሎት ጥራትና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ የማህበረሰብ መሪዎችና አጠቃላይ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ይበልጥ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ማሞ ቱሲ፤ በበኩላቸው ለፍትህ ስርአቱ ጥራትና ፍትሃዊነት የሁሉም አካላት ትብብርና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም ደግሞ ለፍትህ ስርአቱ መስፋት፣ ሚዛናዊና ተአማኒ አገልግሎት ለመስጠት የማህበረሰብ መሪዎች የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።
በመሆኑም ለተሻለ የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት የመንግስት ጥረት እንዳለ ሆኖ የህብረተሰቡ ተሳትፎና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ከመድረኩ የሳታፊዎች መካከል የምስራቅ ሸዋ ዞን ሀገረስብከት የስብከተ ወንጌል ሃላፊ አባ ሃይለገብሬኤል ተስፋ፤ ሁላችንም የትክክለኛ ፍትህ አጋዦች መሆን አለብን ብለዋል።
የአዳማ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሃላፊ ሼህ ማሕሙድ ሁሴን፤ በየትኛውም አጋጣሚና በምንም ሁኔታ እውነትን ብቻ መናገርና መመስከር የግድ መሆኑን ገልጸዋል።
የሀሰት ምስክርነትና በመዋሸት ፍትህ እንዲዛባና ሰዎች እንዲጎዱ ማድረግ በፈጣሪም ዘንድ የሚያስጠይቅ መሆኑን አንስተው ለትክክለኛ ፍትህ አጋዥ ሆነን እንገኝ ብለዋል።
በመድረኩ ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና ሃዳ ሲንቄዎች ተሳትፈዋል።