ቀጥታ፡

ለሀገር ዘላቂ ሰላም ሁነኛ መፍትሄ የሆነው የምክክር ሂደት ለስኬት እንዲበቃ የድርሻችንን እንወጣለን-የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች

አርባምንጭ ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ):- የምክክር ሂደት ለሀገር ዘላቂ ሰላም ሁነኛ መፍትሄ በመሆኑ ለስኬታማነቱ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ በይፋ ስራ ከጀመረ በኋላ ከዝግጅት ምእራፍ ተነስቶ የምክክር ምእራፍ እስከሚደርስ ድረስ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል።

ከሀገር ቤት እስከ ውጭ ሀገር ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ አጀንዳቸውን እንዲያቀርቡና እንዲመክሩ በማድረግ ስኬታማ ስራ መስራቱም ይታወቃል።

በሀገር ጉዳይ አካታችና አሳታፊ በሆነ መልኩ ሁሉም መክሮ የጋራ መፍትሄ ለመሻትም የምክክር ኮሚሽኑ በ11 ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ተሳታፊዎችን ለይቶ አጀንዳቸውን ተቀብሏል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች የምክክር ሂደቱ ለሀገር ዘላቂ ሰላም ሁነኛ መፍትሄ በመሆኑ ለስኬታማነቱ የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።

ከሀገር ሽማግሌዎቹ መካከል አቶ ሰዲቃ ስሜ፤ የግጭትና ጦርነት ውጤቱ ኪሳራ እንጂ አንዳችም ትርፍና የሰላም መፍትሄ የማያመጣ በመሆኑ ለንግግርና ምክክር ቦታ መስጠት ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

በሀገር ጉዳይ ላይ በመምከር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እየሰራ ያለው የምክክር ኮሚሽን ስኬታማ መሆን የሚችለው ሁላችንም ስናግዘውና ስንደግፈው ብቻ ነው ብለዋል።

የምክክር ሂደቱ በሀገራችን የግጭትና አለመግባባት ምክንያቶች ሁነው የዘለቁትን ችግሮች በመለየት በዘላቂነት የምንፈታበት መልካም ዕድል ስለመሆኑ አንስተዋል።

በመሆኑም እኛ የሀገር ሽማግሌዎች የምክክር ሂደት ለሀገር ዘላቂ ሰላም ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን በፅኑ በማመን ለስኬታማነቱ የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።

ሌላኛው የጋሞ የሀገር ሽማግሌ አቶ ተፈራ ኦይቻ፤ በሀገር ጉዳይ ላይ በጋራ መክሮ ችግሮችን መፍታት ለሀገርና ለትውልድ የማሰብ የአስታዋይነት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ይህንን ታሪካዊ እድል በመጠቀም በሀገራችን ጉዳዮች ላይ መክረን ሰላምን፣ አብሮነትንና ሀገራዊ አንድነትን ማጥበቅ አለብን ብለዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራው በዜጎች መካከል ያሉ መሠረታዊ ልዩነቶችን በምክክር በመፍታት በዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት የፀናች ሀገር ለመጪው ትውልድ ለማውረስ እንደሚረዳ እምነታቸውን ገልጸዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ሰላምና ልማትን ማምጣት መሆኑን በአግባቡ የተገነዘብን በመሆኑ እስካሁን እያገዝነውና እየደገፍተው መጥተናል ያሉት ደግሞ ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ አቶ አዳሙ ኪሮ ናቸው።

በመሆኑም ይህንን ታሪካዊ ዕድል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አንስተው በምክክሩ የሚታሰበው ስኬት እንዲመጣ ሁላችንም የድርሻችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በይፋ ከተቋቋመ ጀምሮ ከዝግጅት ምእራፍ ተነስቶ በምክክር ምእራፍ እስካሁን በርካታ ተግባራትን ማከናወኑ ይታወቃል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም