በአማራ ክልል በዘንድሮው የበጋ መስኖ እስካሁን ከ268 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ማልማት ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በዘንድሮው የበጋ መስኖ እስካሁን ከ268 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ማልማት ተችሏል
ባህርዳር፤ ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በዘንድሮው የበጋ መስኖ እስካሁን ከ268 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ማልማት መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የመስኖ እና ሆርቲካልቸር ልማት ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ ይበልጣል ወንድምነው፤ በክልሉ የበጋ መስኖ ልማት እንቅስቃሴ ያለበትን ሁኔታ በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በክልሉ የምርት አማራጮችን በማስፋትና ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት የመውጣት ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በዚህም የበልግና መኸር ምርትን ጨምሮ የበጋ መስኖ ልማት በስፋት እየተከናወነ ስለመሆኑ አንስተው ዘንድሮ በበጋ መስኖ 502 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ከተያዘው እቅድ እስካሁን 268 ሺህ 100 ሄክታር መሬት ማልማት ተችሏል ብለዋል።
ከመስኖ ልማቱ 190 ሺህ ሄክታሩ የስንዴ ሰብል መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ ሌላው በተለያዩ ሰብሎች የለማ መሆኑን ገልጸዋል።
በመስኖ ልማቱ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረው ከልማቱ ከ47 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የመስኖ ልማቱ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ገበያን ለማረጋጋት የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
በሰሜን ጎጃም ዞን የሰሜን ሜጫ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ዘውዱ ክፍሌ፤ በመስኖ ለማልማት ካዘጋጁት 2 ሄክታር መሬት ግማሹን በስንዴ ዘር መሸፈናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም ቀሪውን መሬት በሌሎች ሰብሎችና የአትክልት ልማት ለመሸፈን እየተዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል።
በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የጓንጓ ወረዳ አርሶ አደር ተመስገን ሽታሁን፤ በዘመናዊ የመስኖ ልማት ታግዘው ማከናወን ከጀመሩ ወዲህ የተሻለ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ዘንድሮ የተሻለ ዝግጅት አድርገው እያለሙ መሆኑን አንስተው ጥሩ ምርት ሊያገኙ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
በክልሉ ባለፈው ዓመት በመስኖ በ1ኛ እና 2ኛ ዙር ከለማው መሬት 46 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱ ታውቋል።