ቀጥታ፡

በነቀምቴ የከተማ ግብርና ሥራ ስርአተ ምግብን ለማሻሻልና ገበያን ለማረጋጋት ጉልህ አስተዋጾ አድርጓል

ነቀምቴ፤ ታህሳስ 9/2018 (ኢዘኤ)፡-የከተማ ግብርና የአርሶ አደሩን ሥርአተ ምግብ ለማሻሻልና ገበያን ለማረጋጋት ጉልህ አስተዋጾ ማድረጉን የነቀምቴ ከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የነቀምቴ ከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ግርማ ከድር በከተማዋ 1ሺህ 144 ሄክታር መሬት በአትክልትና ሰብል መልማቱን ገልጸዋል።

በተለይ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማቱ የአርሶ አደሩን ስርአተ ምግብ ከማሻሻል ባለፈ ለአካባቢው ገበያ መረጋጋት ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል።

በከተማ ግብርና በኢኒሼቲቭ የተተገበሩት የወተት ልማት፣ የከብት ማድለብና የዶሮ እርባታ ሥራዎች የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደጉንም ጠቁመዋል።

የከተማ ግብርና ሥራ ነዋሪዎች ባላቸው አነስተኛ ቦታ አትክልት በማልማትና እንስሳትን በማርባት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማስቻል ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ገበያ እያረጋጉ መሆኑን አክለዋል።

በነቀምቴ ከተማ በልማቱ እየተሳተፉ ካሉ ነዋሪዎች መካከል የሶርጋ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ተመስገን ስጦታው ባላቸው አንድ ሄክታር መሬት ላይ የፍራፍሬ ችግኞችን በማልማትና ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር አርሶ አደሩ በፍራፍሬ ልማት ላይ ያለውን ግንዛቤ በማሳደጉ ለሥራቸው መስፋፋት ጉልህ ሚና መጫወቱንም ጠቁመዋል።

በዚህም ቀደም ብለው የተከሏቸው የፍራፍሬ ችግኞች ፍሬ መስጠት እንደጀመሩና የአካባቢውን ገጽታ መቀየራቸውን  አክለዋል።

የከተማ ግብርና ሥራ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እያገዘ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ቶሎሳ ቂናጢ ናቸው።

እሳቸውም በጓሮ እትክልት ልማት በመሰማራት ቤተሰባቸውን የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ከመቻላቸው በለፈ ለገበያ በማቅረብ በኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደጋቸውን ተናግረዋል።

በከተማ ግብርና ሥራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ከግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ ክትትልና ድጋፍ እንዲሁም ግብአት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም