ቀጥታ፡

በሚዛን አማን ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተገልጋይን እንግልት አስቀርቷል

ሚዛን አማን፤ታኅሳሥ 9/2018 (ኢዜአ)፦መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተገልጋይን እንግልት ያስቀረ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በከተማዋ ኢዜአ ያናገራቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች እንዳሉት፥ አገልግሎቱ አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም በተለያዩ ቢሮዎች ሲኬድ ይባክን የነበረ ጊዜና ገንዘብ ለመቆጠብ አስችሏል።

በሚዛን አማን ከተማ ባለፈው ጥቅምት ወር ወደሥራ የገባው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አስመልክቶ ኢዜአ ካነጋገራቸው ተገልጋዮች መካከል አቶ ኪዳኔ ኮይንስ እንዳሉት፥ አገልግሎቱ መንግሥት ለሕዝብ ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ተግባራዊ ምላሽ የሰጠበት ነው።

የማዕከሉ ሥራ መጀመሩ ከዚህ ቀደም አንድን ጉዳይ ለማስፈጸም ሲገጥማቸው የነበረን እንግልት በማስቀረት ጉዳያቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከጥሩ መስተንግዶ ጋር ለማስፈጸም እያስቻላቸው በመሆኑ አገልግሎቱ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

"ከመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጊዜና ጉልበት የቀነሰ ፈጣን አገልግሎት አግኝቺያለሁ" ሲሉ የተናገሩት ደግሞ ሌላዋ ተገልጋይ ወይዘሮ አመለወርቅ ኃይሉ ናቸው።

"በቴክኖሎጂ ተደግፎ ያለውጣ ውረድና ቀጠሮ አገልግሎት የማግኘት ሥርዓት መዘርጋቱ ተጠቃሚ አድርጎናል፤ በዚህም ደስተኛ ነኝ" ያሉት ተገልጋዩዋ፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ በሌሎች አካባቢዎችም መስፋፋት አለበት ብለዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግሥት አገልግሎትን በዝምድናና በእጅ መንሻ የመፈጸም ብልሹ አሠራርን ጭምር እንዳስቀረ የተናገሩት ደግሞ አቶ አዲሱ ገብረጊዮርጊስ የተባሉ ተገልጋይ ናቸው።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ አህመዲን አወል እንደገለጹት፣ ማዕከሉ ለአገልግሎት ክፍት ከሆነበት ጥቅምት አጋማሽ ጀምሮ ከ4 ሺህ 800 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በዲጂታል የታገዘ አገልግሎት ሰጥቷል።

በማዕከሉ 35 አገልግሎቶች በዘጠኝ የክልልና የፌዴራል ተቋማት እንደሚሰጡ ጠቅሰው ተግባሩን ለማጠናከር የዳታቤዝ እና መሰል የቴክኖሎጂ ሥራዎች ማስፋፊያ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የመሶብ አገልግሎትን በክልሉ ለማስፋፋት በተቀመጠው ግብ በአጭር ጊዜ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ 10 መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎች ግንባታ ሥራ መጀመሩንም አቶ አህመዲን ጠቁመዋል።

በመደመር መንግሥት ለማሳካት ከተያዙ የአንድ ግቦች መካከል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተጠቃሽ ሲሆን በዚህም በእያንዳንዱ ከተማ አንድ ማዕከል በመገንባት ብልሹ አሠራርን ለማስቀረት ትኩረት ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም