በከተሞቹ የሰፈነው ሰላም ለመሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት መስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በከተሞቹ የሰፈነው ሰላም ለመሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት መስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ አስችሏል
ባህር ዳር፤ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፦በአካባቢያቸው ሰላም መስፈኑ ለመሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት ትኩረት ሰጥተው በመስራት ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ እንዳስቻላቸው የደሴና የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደሮች ገለጹ።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት እንደገለጹት በከተማው የሰፈነው ሰላም ዘንድሮ ከ200 በላይ አልሚ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዲወስዱ አስችሏል።
በተለይም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱት ውስጥ ከ160 በላይ የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች በተደረገላቸው ድጋፍ የግንባታ ስራቸውን አጠናቀው ማሽን ከውጭ እያስገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም 18 ኢንዱስትሪዎች በያዝነው በጀት ዓመት ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ በተደረገ የተጠናከረ ድጋፍ እስካሁን አራቱ ወደ ማምረት ተሸጋግረዋል ብለዋል።
ወደ ማምረት ከተሸጋገሩት ውስጥም የምግብ ማቀነባበሪያ፣ የፕላስቲክና ሌሎች ፋብሪካዎች እንደሚገኙበት አቶ በድሉ ጠቁመዋል።
ደብረ ብርሃን ከተማ ለአዲስ አበባ ባላት ቅርበትና ሰላም የሰፈነባት በመሆኑ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፤ ከተማ አስተዳደሩም የሚመጡ ባለሃብቶች በፍጥነት የሚስተናገዱበት አሰራር ዘርግቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በወተት ልማት፣ በዳልጋ ከብት ማድለብ፣በመኖ ማቀነባበርና በሌሎች አምራች ኢንዱስትሪዎች ለመሰማራት ለሚመጡ ባለሃብቶች በራቸው ክፍት መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፥ በደሴና አካባቢው ሰላም በመረጋገጡ ከተማ ለቱሪዝም፣ ለንግድና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንድትሆን አድርጓታል።
በዚህም የመጀመሪያውን ዙር የኮሪደር ልማት በስኬት ገንብቶ በማጠናቀቅ ሁለተኛው ዙር መጀመሩን ጠቁመው፥ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችና ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎችም እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
ሰላም በመስፈኑ በእያንዳንዱ ቀን በከተማዋ የተለያዩ ስብሰባዎች እየተካሄዱ መሆኑንና በዚህም ደሴን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ከተማ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በኮሪደር ልማቱ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ራሱን፣ ቤተሰቡንና ሀገሩን እንዲጠቅም ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውንም አስረድተዋል።
እንደ ከንቲባዎቹ ገለጻ፥ በከተሞቹ በልማት ተጨባጭ ውጤት ሊመጣ የቻለው ጽንፈኛው ሃይል የህዝብን ሰላም ለማደፍረስ የሚያደርገውን ሙከራ ከህብረተሰቡና ከጸጥታ አካሉ ጋር በመተባበር በተደጋጋሚ በማክሸፋቸው ነው።