ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን ችላ ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ተሸጋግራለች

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን ችላ ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ መሸጋገሯን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) ገለጹ።

“የኢትዮጵያ የስንዴ ትራንስፎርሜሽን” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ተመርቋል።

ዘጋቢ ፊልሙ በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የፊልም ባለሙያዎች የተዘጋጀ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግብርናን በማዘመንና ራስን ለመቻል የምታደርገውን ስኬታማ ተግባር በሚገባ የሚያሳይ መሆኑ በምርቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።


 

ታሪኩ የተዋቀረው በኢትዮጵያ 'የስንዴ አብዮት' ዙሪያ ሲሆን፤ በኦሮሚያ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች ላይ ያተኮረ ነው።

በዘጋቢ ፊልሙ ላይ ገጸ ባህሪው ዮሐንስ፥ ግዙፍ የጭነት ተሽከርካሪን እያሽከረከረ የሀገርን ቀለብና የወደፊት ተስፋ የሆነውን ምርት በሚያጓጉዝበት ወቅት ከእውነተኛ ገበሬዎችና ባለሙያዎች ጋር ይገናኛል።

በአፍሪካ ታላቅ የስንዴ አምራች ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ ይህንን ጥልቅ የሆነ ትራንስፎርሜሽን በምታከናውንበት በዚህ ወቅት ይህ ታሪክ ከስኬቱ ጀርባ ያለውን የሰው ልጅ ጥረትና ጥንካሬ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይም ነው።


 

ዘጋቢ ፊልሙ ማራኪ የሆኑ የመልክዓ ምድር ዕይታዎችን ከጥልቅ የታሪክ አወቃቀር ጋር በማዋሃድ፣አርሶ አደሮች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከሚተገብሩባቸው እርሻዎች ጀምሮ ምርቶቹ እስከሚደርሱበት የከተማ ማዕከላት ድረስም ያስቃኛል።

ፊልሙ ስለ ስንዴ ምርት ብቻ የሚተርክ ሳይሆን ስለ ጽናት፣ ስለ ፈጠራ እና ራሷን ችላ ለአፍሪካ የጋራ ብልጽግና አርአያ ለመሆን በመገስገስ ላይ ስላለች ሀገር የሚተርክ ድንቅ የኪነ-ጥበብ ሥራ ነው።


 

የዘጋቢ ፊልሙ ታሪክ የሚያተኩረው በሦስት ዋና ዋና ምዕራፎች ላይ በዚህም ኢትዮጵያ ለዓመታት ለስንዴ ግዥ የምታወጣው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እና ይህን ለመቀየር የፖለቲካ ቁርጠኝነት የታከለበት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እንዴት እንደተጀመረ እና አርሶ አደሩ እንዴት በኩታ ገጠም እርሻ እንደተሰለፈ የሚያስቃኝ ነው።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከጠባቂነት ወጥታ ስንዴን ወደ ውጭ መላክ የጀመረችበት ድንቅ ስኬትም የሚያስቃኝ ነው።

ዘጋቢ ፊልሙ ጥራቱን ጠብቆ የተሰራ ሲሆን ለዓይን የሚማርኩ የኢትዮጵያ እርሻዎች፣ የአዝመራ አሰባሰብ ሂደቶች እና የአርሶ አደሩ የደስታ ስሜትንም ያካተተ ነው።

ዘጋቢ ፊልሙ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት የደረሰችበትን ድንቅ ስኬት እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም የኢትዮጵያን ተሞክሮ በማየት መነሳሳት የሚፈጥሩበትም ነው።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን ችላ ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ተሸጋግራለች።

ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት የስንዴ ምርት ከውጭ ስታስገባ መቆየቷን ገልጸው፤ ይህንን ታሪክ ለመቀየርና ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን ከመቻል አልፋ ለሌሎች እንድትተርፍ ለማስቻል የተቀረጸው ስትራቴጂ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቅሰዋል።

በቁርጠኝነት ተግባራዊ የተደረገው የኩታ ገጠም እርሻ አሠራር ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ጠቁመው፥በአሲዳማነት የተጠቁ በርካታ ሄክታር መሬቶችን በኖራ በማከም ወደ ምርት እንዲገቡ የማድረግ ሥራዎችም ለውጤታማነቱ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን አስረድተዋል።

ረግረጋማ የሆኑ የደጋ ቦታዎችን በቴክኖሎጂ በማድረቅ ለምርት እንዲውሉ ማድረግ ሌላኛው መሠረት መሆኑን ጠቅሰው፥ በበርካታ ሄክታር መሬት ላይ እየለማ የሚገኘው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለሀገር ውስጥ ብሎም ኢትዮጵያ የስንዴ ምርትን ወደ ውጪ እንድትልክ ማስቻሉን ገልጸዋል።

ዘጋቢ ፊልሙ የኢትዮጵያ የስንዴ ምርት ድልን በመረጃና በምስል ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍና ወጣቶች ወደ ግብርናው ዘርፍ በስፋት እንዲገቡ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም