ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የግብርና ብድር አስጀመረ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዘላቂ ግብርናን ለመደገፍና የገጠር ኢኮኖሚ እድገትን ለማጎልበት ለአርሶና አርብቶ አደሮች የግብርና ብድርን በይፋ አስጀምሯል።

የባንኩ የኮርፖሬት አገልግሎቶች ምክትል ፕሬዝዳንት ኤፍሬም መኩሪያ በወቅቱ የብድር አገልግሎቱ የአነስተኛ ባለ-ይዞታ አርሶና አርብቶ አደሮች የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።


 

አገልግሎቱ አርሶ አደሮች በግለሰብ ደረጃም ሆነ ተደራጅተው ከግብርና ግብዓቶች እስከ ማሽነሪዎች ግዥ የብድር አገልግሎት የሚያገኙበት መሆኑን ገልጸዋል።

ለእንስሳት ምርታማነት አርብቶ አደሮች የተለያዩ ግብዓቶች ለማሟላት ዕድል የፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።

አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ቅርንጫፍ በመሄድ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ተመላክቷል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የግብርና ፋይናንስ በማሳደግ የገጠር ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡


 

መንግስት የግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉትን በርካታ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል፡፡

ከዚህ ውስጥ አካታች የሆነ የፋይናንስ ተደራሽነትን በገጠር ማረጋገጥ መሆኑን ገልጸው፤ ዛሬ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይፋ ያደረገው የብድር አገልግሎት አንዱ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ባንኩ ለአርሶ አደሩና ለአርብቶ አደሩ የጀመረው አገልግሎት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም