የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ቴክኖሎጂን የመጠቀም አቅማችንን አሳድጓል-ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ቴክኖሎጂን የመጠቀም አቅማችንን አሳድጓል-ተማሪዎች
ጅግጅጋ፣ታህሳስ 9/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ቴክኖሎጂን የመጠቀም አቅማቸውን እንደጨመረላቸው በጅግጅጋ ስልጠናውን የወሰዱ ተማሪዎች ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢንሼቲቭ በመላው ሀገሪቷ የተጀመረው የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በቴክኖሎጂ የበቃና ተወዳዳሪ የሰው ሀይልን ለማፍራት አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመው ሀገር አቀፍ ስልጠና ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግም አበርክቶው የላቀ ነው።
ስልጠናውን የሁለተኛ ደረጃ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የመንግስት ሰራተኞች እና ወጣቶች በንቃት እየተከታተሉ መሆናቸውም ታውቋል።
በሱማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማም በርካታ ተማሪዎችና መምህራን ስልጠናውን የወሰዱ ሲሆን ፤ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የእድሉ ተጠቃሚዎች ስልጠናው የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን ማሳደጉን ተናግረዋል።
በከተማው የካህ ቁጥር አንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሙስጠፌ ሀሰን የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናን በበይነ መረብ ወስዶ በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ሰርተፊኬት ማግኘቱን ገልጿል።
በስልጠናውም በራሱ ላይ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክህሎቱን እንዳሳደገው ተናግሯል።
የመጀመሪያዎቹን ሁለት ኮርሶች ከጨረስኩኝ በኋላ ሌሎች 20 ተማሪዎችን የፕሮግራሙን ጠቀሜታ በማስረዳት ማስመዝገቡን የተናገረው ተማሪ ሙስጠፌ፤ በተለይም ወጣቶች ይህንን ነጻ የትምህርት ዕድል መጠቀም እንዳለባቸው ተናግሯል።
ተማሪ አስማ አሊ በበኩሏ፥ ከኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በዳታ አናሊሲስ ሰርተፊኬት ማግኘቷን ገልጻለች።
ይህንን ስልጠና ከመውሰዷ በፊት እና ዛሬ ከፍተኛ ልዩነት መኖሩን አንስታ፤ ስልጠናው የተማሪዎችን እውቀትና ክህሎታቸውን እንደሚያሳድገው ተናግራለች።
የኢትዮ ኮደርስ ፕሮግራም ወጣቶች የቴክኖሎጂ አቅማቸውን በማሳደግ ያላቸውን እውቀት ለሀገራቸው ዲጂታል እድገት እንዲያበረክቱ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጻለች።
ተማሪ አቡበከር መሀመድ ሀሰን የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የወሰደ መሆኑን ገልፆ፥ በተለይ ዳታ አናሊሲስ ላይ ትኩረት መስጠቱን ተናግሯል።
ስልጠናው ከዲጂታል ዓለም ጋር መጓዝ እንደሚያስችል ተናግሮ፤ከራሱ አልፎ ለሌሎች ተማሪዎችም ድጋፍ መስጠት እንዲችል ማገዙን ገልጿል።
የካህ ቁጥር አንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ከድር ረሺድ በበኩላቸው፥ ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በ2017 በትምህርት ቤቱ መጀመሩን ተናግረው ይህንን ስልጠና ተማሪዎች እንዲወስዱ ትኩረት አድርገን ሰርተናል ብለዋል።
ከዚህ በፊት እንዲህ አይነት እድል ውስን እንደነበር ገልጸው፥በአሁኑ ወቅት እድሉ በቤታችሁ ድረስ በመምጣቱ ወጣቶች እድሉን መጠቀም አለባችሁ የሚል ምክር አስተላልፈዋል።
በትምህርት ቤቱ በአንዴ 40 ተማሪ ማስተናገድ የሚችል አይሲቲ ላብ ክፍል መኖሩን ገልጸዉ፥ ተማሪዎች የቴክኖሎጂ አቅማቸውን በማስፋት በቤት ሆነው በአለም ዙሪያ ያለውን ሥራ መስራት የሚያስችላቸውን አቅም እንደሚፈጥርላቸውም ገልጸዋል።