ቀጥታ፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የህክምና ግብአት ሽፋንን በማሳደግ የጤና አገልግሎትን ማሻሻል ተችሏል - ጤና ሚኒስቴር

አሶሳ፤ ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፦ በሀገር አቀፍ ደረጃ የህክምና ግብአት የሆነውን ኦክስጂን ሽፋን በማሳደግ በጤናው ዘርፍ የሚሰጠውን አገልግሎት ማሻሻል መቻሉን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ሀገር አቀፍ የህክምና ኦክስጂን የምክክር ዐውደ ጥናት በአሶሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣ የሁሉም ክልሎች ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ ሆስፒታሎች ስራ አስኪያጆች እና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።


 

የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ አክሞ ማዳን የሚያስችል የጤና አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ በመተግበር ላይ ይገኛል።

ይህም ጥራቱ የተጠበቀ እና ፍትሃዊ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዝ ከመሆኑም በተጨማሪ መሠረታዊ የህክምና መሳሪያዎች ተደራሽ እንዲሆኑ አድርጓል ብለዋል።

ከአምስት ዓመት በፊት የነበረውን ሶስት የኦክስጂን ማዕከል በአሁኑ ሰዓት ወደ 85 በማድረስ ዜጎች ህክምናውን በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ በማድረግ በኦክስጂን እጥረት የሚከሰተውን ሞት መቀነስ ተችሏል ብለዋል።


 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ወልተጂ በጋሎ በበኩላቸው፤ በአሶሳ ሆስፒታል የተተከለው የኦክስጂን ማምረቻ ማዕከል ከሆስፒታሉ በተጨማሪ በክልሉ ጤና ተቋማት ምርቱን በማቅረብ ህብረተሰቡ የተቀላጠፈ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ አስችሏል ብለዋል።

የምክክር መድረኩ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም