የኮንሶዎች እርከን ሥራ ለተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ጉልህ አስተዋጾ እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኮንሶዎች እርከን ሥራ ለተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ጉልህ አስተዋጾ እያበረከተ ነው
ካራት ፤ ታህሳስ 9/2018(ኢዜአ)፡-በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበው የኮንሶዎች እርከን ሥራ ለተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ጉልህ አስተዋጾ ያበረከተ ሀገር በቀል እውቀት መሆኑ ተገለጸ፡፡
የኮንሶ መልክአ ምድር በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በ2003 ዓ.ም በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ የሚታወስ ነው።
መልክአ ምድሩ በ23 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈና በውስጡ በርካታ ቅርሶችን የያዘ ሲሆን የእርሻ እርከኖች፣ ጥብቅ ደኖች፣ ኩሬዎችና መንደሮች ይገኙበታል፡፡
የኮንሶ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ሃላፊ ወይዘሮ ገንዘቤ ኮራ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበው የኮንሶዎች እርከን ሥራ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ ያለ ሀገር በቀል አውቀት ነው።
ባህላዊ የእርከን ሥራው የኮንሶ ማህበረሰብ የታታሪነት ምልክት መሆኑን ገልጸው፣ ማህበረሰቡ አስቸጋሪ መልክአ ምድርን ጭምር በማልማት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ያሳየበት እንደሆነም ተናግረዋል።
የእርከን ሥራው ኮንሶዎች ትውልድን የተሻገረ ቅርስና ተፈጥሮን ለመጠበቅ የዘየዱት ሃገር በቀል እውቀት ሲሆን የአፈር መሸርሸርን ከመከላከል ባለፈ የዝናብ ውሃን ወደመሬት በማስረግ ለምርትና ምርታማነት ማደግ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
እንደ ሃላፊዋ ገለጻ በአካባቢው ከአዝርዕት ሰብሎች በቆሎ፣ ማሽላ፣ ጤፍ፣ ቦሎቄ እና ዳጉሳን እንዲሁም የጓሮ አትክልቶች በተለይ በመኸርና በበልግ ወቅቶች በስፋት ይመረታሉ።
በጥምር ግብርና የሚተዳደሩት ኮንሶዎች ተፈጥሮን ጠብቀው በስፋት ለሚያከናውኑት የእንስሳት እርባታ ስራም ከሰብል ተረፈ ምርት በተጨማሪ የመኖ ዛፎችን እንደሚያለሙም ተናግረዋል።
የኮንሶ ዞን ህዝብ የባህል አባት ካላ ገዛኸኝ ወልዳዊት በበኩላቸው የኮንሶዎች ባህላዊ የእርከን ሥራ የህዝቡ የአኗኗር ዘይቤ መገለጫና የሀገር በቀል ዕውቀት ውጤት ነው ብለዋል።
የጥንት ኮንሶዎች የስልጣኔ ምልክት የሆነው የእርከን ሥራ ከአካባቢው የአየር ጸባይ ጋር እንዴት ተስማምቶ መኖር እንደሚቻል ትውልድ የተማረበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የእርከን ሥራው አፈር እንዳይሸረሸር እንዲሁም ለምነትና እርጥበቱ ተጠብቆ እንዲቆይ በማድረግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የማይተካ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።
የኮንሶ ማህበረሰብ ባህላዊ የእርከን ሥራ ከመኖሪያ መንደር ጀምሮ እስከ አርሻ ማሳ በጥንቃቄ የሚሠራ የህልውና መገለጫ ነው ያሉት ደግሞ አቶ ሮባ ለሚታ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ናቸው።
ያለን ትልቁ ሀብት መሬት ነው ያሉት አስተያየት ሰጪው እርከን ሥራም መገለጫችን ነው ብለዋል።
የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ መጠበቅ ካልተቻለ ትውልድ የማስቀጠል ጉዳይ አደጋ እንደሚገጥመው ገልጸው፣ "ከአባቶች የተረከብነውን ቅርስ ጠብቀን ለልጆቻችን እናስተላልፋለን" ብለዋል።
የኮንሶ የመሬት አቀማመጥና የአየር ጸባይ ምቹ ባይሆንም አባቶች እርከን በመስራትና በባህላዊ ኩሬ ውሃ በማቆር ተፈጥሮን ተቋቁሞ መኖር የሚቻልበትን ዘዴ እንዳስተማራቸው ገልጸዋል፡፡
የኮንሶ ማህበረሰብ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን ያለውን ጠቀሜታ ቀድሞ መገንዘቡን የገለጹት አቶ ሮባ፣ በዚህም የተፋሰስ ሥራ በማከናወን ለምርታማነት መረጋገጥ የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
የኮንሶዎች ሀገር በቀል ዕውቀት ውጤት የሆነው የእርከን ሥራ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ አካባቢዎችም በስፋት እየታየ ነው።