ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

አምቦ፤ ታህሳስ 9/2018(ኢዜአ):-በኦሮሚያ ክልል የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ።

በምዕራብ ሸዋ ዞን የማህበረሰብ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማሳደግና አገልግሎቱን ወደአንድ ማዕከል ለማምጣት ያለመ የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡  

በመድረኩ በክልሉ ጤና ቢሮ የሀብት አሰባሰብና የማህበረሰብ ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ ድንቁ ኢረና ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ህብረተሰቡ በቀበሌና በወረዳ ደረጃ ሲጠቀም የነበረውን የጤና መድህን አገልግሎት በዞን ደረጃ በማሳደግ በአንድ ማዕከል ለመምራት ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰራ ቆይቷል።


 

እንደ ክልል አገልግሎቱን ወደ አንድ ማዕከል የማምጣቱ ሥራ በቦረና ዞን መጀመሩን አስታውሰው በአሁኑ ወቅትም በምዕራብ ሸዋ ዞን የተጀመረውን ጨምሮ ወደ 16 ዞኖች ከፍ ማለቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የማህበረሰቡን የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት በወረዳና በቀበሌ ደረጃ ሲሰጥ የነበረው አገልግሎት ክፍተት እንደነበረበት ያስታወሱት አቶ ድንቁ፣ አገልግሎቱ በዞን ደረጃ በአንድ ማዕከል እንዲመራ መደረጉ ጠንካራ የፋይናንስ ስርአት በመፍጠር የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ይረዳል ብለዋል።


 

የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ በበኩላቸው፤ ከዞኑ 23 ወረዳዎች ለጤና መድህን አገልግሎት ከህብረተሰቡ የሚሰበሰበው ገንዘብ ወደ አንድ ማዕከል መምጣቱ ሁሉም ወረዳዎች በፍትሃዊነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይረዳል ብለዋል፡፡

አገልግሎቱ በዞን ደረጃ ወደ አንድ ማዕከል መምጣቱ ከህብረተሰቡ የሚሰበሰበውን ገንዘብ ለሚፈለገው ዓላማ ለማዋልና የመድሀኒት አቅርቦትን በማሻሻል ለህብረተሰቡ ቀልጣፋና የተሻለ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ሲሉም አስረድተዋል።

የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት በዞን ደረጃ በአንድ ማዕከል መደረጉ ብልሹ አሰራሮችን በማስቀረት ህብረተሰቡ ታአማኒነት ያለው የጤና አገልግሎት እዲያገኝ ያደርጋል ያሉት ደግሞ የዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በየነ ናቸው፡፡


 

እንደኃላፊው ገለጻ ህብረተሰቡ በገንዘብ እጥረት ያገኛቸው ያልነበሩ የጤና አገልግሎቶችን በማህበራዊ ጤና መድህን አገልግሎት በፍትሀዊነት ተጠቃሚ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው። 

የመድረኩ ተሳታፊዎችም በቀበሌና በወረዳ ደረጃ የነበረውን የጤና መድህን አገልግሎት በዞን ደረጃ ለማሳደግ የተጀመረው ሥራ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ስለሚያደርግ ለስኬታማነቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ የሜታ ሮቢ ወረዳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ተሾመ፤ ከመድረኩ ስለ ጤና መድህን ኢንሹራንስ ጠቀሜታ የተሻለ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ 

ለአንድ ቀን በተካሄደው በዚህ መድረክ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ ሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸው ታውቋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም