የአየር ኃይል የምስረታ በዓል ተቋሙ የደረሰበትን ደረጃ በሚያሳይ መልኩ ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ኃይል የምስረታ በዓል ተቋሙ የደረሰበትን ደረጃ በሚያሳይ መልኩ ይከበራል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፡- 90ኛው የኢፌዲሪ አየር ኃይል የምሰረታ በዓል አየር ኃይሉ የደረሰበትን ደረጃ በሚያሳይ እና በሚመጥን መልኩ እንደሚከበር የአየር ኃይል ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ነገራ ሌሊሳ ገለጹ።
የኢፌዲሪ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን የተመለከተ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።
የአየር ኃይል ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ነገራ ሌሊሳ በዚሁ ወቅት አየር ኃይል ረጅም እድሜ ካላቸው ተቋማት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
የበዓሉ ዓላማ አየር ኃይሉ ያለፋቸውን ተጋድሎዎች እና የተከፈለውን ዋጋ ለመዘከርና ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ተቋሙ ቀዳሚ አየር ኃይል ለመሆን እያከናወነ ያለውን ስራ ለማሳየት መሆኑን ጠቁመዋል።
አየር ኃይል የኢትዮጵያን ነጻነት አስጠብቆ ዛሬ ላይ ማድረሱን ጠቅሰው፤ ከለውጡ ወዲህ ራሱን በሰው ኃይል፣ በትጥቅ እንዲሁም በመሰረተ ልማት ማደራጀቱን ጠቁመዋል።
90ኛው የኢፌዲሪ አየር ኃይል የምስረታ በዓል አየር ኃይሉ የደረሰበትን ደረጃ በሚያሳይ መልኩ እንደሚከበር ጠቁመዋል።
በበዓሉ የተለያዩ ሀገራት የሚሳተፉበት የአየር ላይ ትርኢት፣ የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ኮንፈረንስና የአቪዬሽን ኤክስፖ እንደሚካሄድ አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድር በበኩላቸው፤ አየር ኃይል የሀገር ኩራት እና የህዝብ መከታ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን የነጻነት ታሪክ አጽንተው ካቆሙ ተቋማት መካከል አንዱ የአየር ኃይል መሆኑን አንስተዋል።
በተጨማሪም የተለያዩ የሰው ሰራሽ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት ህዝብን ከአደጋ የጠበቀ ተቋም መሆኑን ጠቁመዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ባደረገው ሪፎርም አቅሙን በማሳደግ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ሌት ተቀን በሚስጠበቅ ላይ የሚገኝ የሀገር ሀብት የሆነ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።