የኢትዮጵያና ህንድ ስትራቴጂክ አጋርነት ያላቸውን ዓለም አቀፍ ተሰሚነት በሚገባ እንዲጠቀሙ ትልቅ እድል ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ህንድ ስትራቴጂክ አጋርነት ያላቸውን ዓለም አቀፍ ተሰሚነት በሚገባ እንዲጠቀሙ ትልቅ እድል ይፈጥራል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያና ህንድ ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት ማሳደጋቸው ያላቸውን አህጉራዊ ሚናቸውን በመጠቀም የታዳጊ ሀገራትን ፍላጎት ለማስከበር ትልቅ እድል እንደሚፈጥር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ ያደረጉትን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ተከትሎ፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው የረጅም ዘመን ያስቆጠረ የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማደጉ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።
በምክር ቤት ንግግራቸው ህንድና ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ በተለያዩ ዘርፎች በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት ማደጉ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
የምክር ቤት አባል ነጃት ግርማ (ዶ/ር) ሁለቱ ሀገራት የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተዋል።
ይህን ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር ለህዝቦቻቸው የጋራ ብልጽግና ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ማንሳታቸውን ተናግረዋል።
ሌላኛው የምክር ቤት አባሉ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያና ህንድ ቀደምት የስልጣኔ ባለቤት እንደመሆናቸው የቀጣይ ዕጣ ፋንታቸው በእጃቸው ላይ ነው ብለዋል።
የሀገራቱ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት ማደጉ በምንም ሁኔታ የማይናወጥ ወዳጅነት መመስረት ያስችላቸዋል ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝትም የሀገራቱ ግንኙነት የበለጠ መጠናከሩን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
አጋርነቱ በዓለም አቀፍ መድረኮች እርስ በእርስ ለመደጋገፍ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የገለፁት ደግሞ ሌላው የምክር ቤት አባል አምባሳደር ቶፊቅ አብዱላሂ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን አህጉራዊ ተጽዕኖ በመጠቀም የታዳጊ ሀገራትን ፍላጎት ለማስከበር በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ህንድ ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን እ.ኤ.አ በ1948 የጀመሩ ሲሆን፣ አሁን የደረሱበት የስትራቴጂክ አጋርነት ደረጃ ለሁለቱ ህዝቦች የጋራ ብልጽግና አዲስ ተስፋ የሰነቀ መሆኑ ተመላክቷል።