በጼጼ የዶሮ ብዜት፣ ስርጭትና የመኖ ማቀነባበሪያ ማዕከል የሥራ ዕድል ተፈጥሮልናል - ኢዜአ አማርኛ
በጼጼ የዶሮ ብዜት፣ ስርጭትና የመኖ ማቀነባበሪያ ማዕከል የሥራ ዕድል ተፈጥሮልናል
አሶሳ፤ ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፦ የጼጼ የዶሮ ብዜት፣ስርጭትና የመኖ ማቀነባበሪያ ማዕከል በተለያዩ የሙያ መስኮች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የአካባቢው ሰዎች ተናገሩ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኡራ ወረዳ የሚገኘው ጼጼ የዶሮ ብዜት፣ ስርጭትና የመኖ ማቀነባበሪያ ማዕከል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብረሃም በላይ (ዶ/ር) እና የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋን ጨምሮ የፌዴራል እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተመርቋል።
ማዕከሉ የመስራች ዶሮዎች ማሳደጊያ እና እርባታ፣ በ45 ቀናት ውስጥ 115 ሺህ ጫጩቶችን ማስፈልፈል የሚያስችል የጫጩት ማስፈልፈያ ማሽን፣ የእንቁላል ጣይ ዶሮ እርባታ እና በሰዓት 60 ኩንታል መኖ ማዘጋጀት የሚችል የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽንን ያካተተ ነው።
ከ34 በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ሰዎችም በማዕከሉ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል።
በማዕከሉ የእንስሳት እርባታ ባለሙያ የሆነው ጀማል ሙሀመድ በማዕከሉ ባገኘው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆኑን ገልጿል።
በቀጣይ ከማዕከሉ የሚመረተውን እንቁላል እና ዶሮ ለማህበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።
ሳይንሱን በጠበቀ መልኩ የዶሮ መኖ በማዘጋጀት እና በማቅረብ እንዲሁም ዶሮዎችን በመንከባከብ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሆነም ተናግሯል።
ሌላው በማዕከሉ የዶሮ ተንከባካቢ በመሆን የሥራ ዕድል የተፈጠረለት ወጣት ናስር ማናሲ ማዕከሉ በዶሮ እርባታ የጀመረው ስራ ለአካባቢው ማህበረሰብ ትልቅ ጥቅም የሚሰጥ ነው ብሏል።
በቀጣይ ከማዕከሉ በሚያገኘው የሥራ ልምድ የዶሮ እርባታ ስራ ለመጀመር ዕቅድ እንዳለው ተናግሯል።
ጼጼ የዶሮ ብዜት፣ ስርጭትና የመኖ ማቀነባበሪያ ማዕከል ስራ አስኪያጅ አብዱረህማን ኡስማን በበኩላቸው ማዕከሉ ከ2017 ነሐሴ ወር ጀምሮ ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰው በማዕከሉ የሚገኙ ዶሮዎች ተገቢውን እንክብካቤ እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።
ማዕከሉ ከ34 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ሰዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን ገልጸው በቀጣይ በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር ተጨማሪ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የዶሮ እና የእንቁላል ስርጭቱን ለማከናወን ወጣቶች በየአካባቢያቸው ተደራጅተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ አሳስበዋል።
በአሁኑ ሰዓት ከ20 ሺህ በላይ ዶሮዎች በማዕከሉ ይገኛሉ።