ኦፓልን ጨምሮ ሌሎች የማዕድን ምርቶችን ለማገበያየት ዝግጅት ተጠናቋል - የኢትዮጵያ ምርት ገበያ - ኢዜአ አማርኛ
ኦፓልን ጨምሮ ሌሎች የማዕድን ምርቶችን ለማገበያየት ዝግጅት ተጠናቋል - የኢትዮጵያ ምርት ገበያ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፡- የኦፓል ማዕድንን ጨምሮ ሌሎች የማዕድን ምርቶችን ማገበያየት ለመጀመር የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መርጊያ ባይሳ ገለጹ።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለኢዜአ እንደገለጹት ምርት ገበያው ግብይትን በማዘመንና በግልጽነት መርሆዎች በመምራት የሀገሪቱን የንግድ ሥርዓት ለማቀላጠፍ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሥራ ሲጀምር በሁለት ምርቶች ማለትም በበቆሎና ስንዴ ግብይት መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡
በሂደት ስራውን ማስፋት የቻለው የምርት ገበያው፤ በአሁኑ ወቅት ቡና፣ ሰሊጥ፣ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች እና ቅመማ ቅመሞችን ጨምሮ የሚያገበያያቸውን የግብርና ምርቶች ወደ 28 ከፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
በተለይ ከለውጡ በኋላ መንግሥት ለምርት ገበያው በሰጠው ትኩረት 15 አዳዲስ ምርቶችን ወደ ግብይቱ ማስገባት መቻሉን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል።
ምርት ገበያው ተወዳዳሪና ተፈላጊ የግብይት መዳረሻ እንዲሆን በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተው፤ በዚህ ምርት ገበያው የበለጠ ውጤታማ እየሆነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አዋጅ ከተሻሻለ በኋላ ተቋሙ ከግብርና ውጭ የሆኑ ማዕድንና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ማገበያየት የሚችልበት ኃላፊነት እንደተሰጠው ዋና ስራ አስፈጻሚው አንስተዋል።
ይህንኑ ተከትሎ የኦፓል ማዕድንን ወደ ገበያ ለማስገባት ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ከኦፓል በተጨማሪ ሌሎች ማዕድናትን ለማገበያየት የሚያስችል ራሱን የቻለ የግብይት ሥርዓት ለመዘርጋት በምርት ገበያው በኩል ሲደረጉ የነበሩ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።
በማዕድን ሚኒስቴር በኩል መጠናቀቅ ያለባቸው ጉዳዮች ሲፈጸሙ የማገበያየት ስራው እንደሚጀመር ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የአርቴዝናል እና ጌጣጌጥ ማዕድን ልማት ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ጌራ ተጫነ (ዶ/ር) በበኩላቸው በጌጣጌጥ ማዕድናት ዘርፍ የሚስተዋሉ የግብይት ችግሮችን ለመፍታትና ዘርፉን በዘመናዊ መንገድ ለመምራት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታወቀዋል።
ይህንን ተከትሎ በኦፓል ምርት የሚስተዋሉ የግብይት ችግሮችን ለመፍታት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር የተጀመረው ሥራ በአሁኑ ወቅት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ምርቱ በቅርቡ ወደ ገበያ እንደሚገባ ጠቁመው፤ አሰራሩ ተግባራዊ መሆኑ ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከልና አምራቾችን ይበልጥ ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው አስታውቀዋል።