ቀጥታ፡

ለገና በዓል ለሚመጡ እንግዶች ምቹ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል- የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 9/2018 (ኢዜአ)፡- የዘንድሮውን የገና በዓል ለማክበር እና ለመጎብኘት ወደ ላሊበላ ከተማ ለሚመጡ እንግዶች ምቹ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

ከቱሪዝም ጋር የተሣሠረውን የከተማዋ ኢኮኖሚ በይበልጥ በማነቃቃት ረገድ የገና በዓል ሚና የጎላ መሆኑን የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መሳይ ወዳጆ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ኢኮኖሚው ከቱሪዝም ጋር መቆራኘቱን የተገነዘበው የከተማዋ ነዋሪም፤ የአካባቢውን ሰላም በማጽናት በእግር፣በመኪናና በአውሮፕላን ለሚመጡ እንግዶች ምቹ አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቷል ብለዋል።

በመንግሥት በኩልም ከከተማዋ ነዋሪዎች፣ ከአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ጋር ውይይቶች መደረጋቸውን እና በየዘርፉ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ለእንግዶች የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም መሠረት ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች፣ ካፍቴሪያዎች እንዲሁም አስጎብኚዎች ምቹ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

እስከ 1 ሚሊየን እንግዶች እንደሚጠበቁ ጠቁመው፤ ይህን ታሳቢ ያደረገ ጊዜያዊ የመፀዳጃ ቤቶች፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እና የመጀመሪያ ሕክምና መስጫ ማዕከሎች ዝግጁ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

እንግዶች በሆቴሎችና በግለሰቦች ቤት ጭምር እንደሚያርፉ ገልጸው፤ በድንኳን ለሚያርፉም ቦታዎችን የማጽዳት፣ ውኃ እና ኤሌክትሪክ እንዲሟላላቸው የማድረግ ሥራም እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በከተማዋ መግቢያ በሮች ወጣቶች እንግዶችን በእግር አጠባ ለመቀበል እና አስፈላጊ ትብብሮችን ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም አመላክተዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ እና የቅዱስ ላሊበላ የልደት ቀን ታኅሣስ 29 በላሊበላ ከተማ በድምቀት እንደሚከበር ገልጸው፤ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ወደ ከተማዋ መጥተው ይህን ደማቅ ዕለት እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም