ቀጥታ፡

በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ይካሄዳሉ።


ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ መቻል ከድሬዳዋ ከተማ ይጫወታሉ።


መቻል በሊጉ ባደረጋቸው 12 ጨዋታዎች ስምንት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ተሸንፏል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 20 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ሰባት ጎሎችን አስተናግዷል።


ቡድኑ በ26 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።


ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው 12 ጨዋታዎች መካከል አራቱን ሲያሸንፍ ሰባት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይቷል።


12 ግቦችን ሲያስቆጥር 18 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ድሬዳዋ በ13 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።


ጨዋታው መቻል ተከታታይ ድሎችን ለማስመዝገብ፣ ድሬዳዋ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።


በሌላኛው መርሃ ግብር ሸገር ከተማ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።


አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በሊጉ 11 ጨዋታዎችን አድርጎ ስምንት ጊዜ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። በጨዋታዎቹ 18 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 10 ጎሎችን አስተናግዷል።


አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሸገር ከተማ በ24 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።


ቦሌ ክፍለ ከተማ በሊጉ ባካሄዳቸው 12 ጨዋታዎች 12 ጨዋታዎች አምስቱን ሲያሸንፍ ሁለት ሽንፈት አጋጥሞታል። በአምስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይቷል።


13 ግቦችን በጨዋታዎቹ ላይ ሲያስቆጥር 10 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ20 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም