ቀጥታ፡

ማንችስተር ሲቲ ለካራባኦ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ አለፈ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 8/2018(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ካራባኦ ዋንጫ  የሩብ ፍጻሜ መርሃ ግብር ማንችስተር ሲቲ ብሬንትፎርድን 2 ለ 0 አሸንፏል።

ማምሻውን በኢትሃድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ራያን ቸርኪ በ32ኛው እና ሳቪኒዮ 67ኛው ደቂቃ ላይ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

በጨዋታው ማንችስተር ሲቲ በተጋጣሚው ላይ ብልጫ ወስዶ ተጫውቷል።

የማንችስተር ሲቲው ተከላካይ አብዱኮዲር ኩሳኖቭ በ16ኛው ደቂቃ ላይ በብሬንትፎርዱ ኬቨን ሻደ የሰራው ጥፋት በቢጫ ካርድ መታለፉ አጨቃጫቂ ነበር።

ሻደ የመጨረሻ ሰው ሆኖ በተሰራው ጥፋት ኩሳኖቭ በቀይ ካርድ መውጣት ነበረበት የሚል ተቃውሞ ብሬንትፎርዶች ቢያሰሙም ውሳኔው ሳይቀለበስ ቀርቷል።

በካራባኦ ዋንጫ በቪዲዮ የታገዘ ዳኝነት (ቫር) የሚተገበረው ከግማሽ ፍጻሜ አንስቶ ነው።

ውጤቱን ተከትሎ ማንችስተር ሲቲ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።

ሲቲ ለካራቦኦ ግማሽ ፍጻሜ ሲያልፍ ከእ.አ.አ 2021 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።


 

በሌላኛው መርሃ ግብር ኒውካስትል ዩናይትድ ፉልሃምን 2 ለ 1 አሸንፏል።

ዮአን ዊሳ እና ሉዊስ ማይሊ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ሳሳ ሉኪች ለፉልሃም ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።

የወቅቱ የካራባኦ ዋንጫ አሸናፊ ኒውካስትል ዩናይትድ ለግማሽ ፍጻሜ አልፏል።

ጨዋታዎቹን ተከትሎ የግማሽ ፍጻሜ ድልድል ወጥቷል።

ኒውካስትል ዩናይትድ ከማንችስተር ሲቲ እና ቼልሲ ከአርሰናል እና ክሪስታል ፓላስ አሸናፊ ጋር ይጫወታሉ።

አርሰናል ከክሪስታል ፓላስ በዚህ ሳምንት ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በመርሃ ግብር መደራረብ በመራዘሙ ምክንያት በቀጣዩ ሳምንት ማክሰኞ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም