በክልሉ ኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ግንባታን ዜሮ ለማድረግ በቁርጠኝነት ይሠራል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ግንባታን ዜሮ ለማድረግ በቁርጠኝነት ይሠራል
አዲስ አበባ፤ታህሳሰ 8/2018 (ኢዜአ)፦በሀረሪ ክልል ኮንትሮባንድ እና የመሬት ወረራና ህገወጥ ግንባታን ዜሮ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተገለፀ።
የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በመደመር መንግስት እይታ የዘርፎች እመርታ ሥልጠና ማጠቃለያ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተሰጠው አቅጣጫ ግቦች አፈፃፀም ዙሪያ ላይ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ላይም በክልሉ በተለይም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፤ የቅዳሜ ገበያን በማስፋፋት አምራችና ሸማችን በማገናኘት እንዲሁም የቁጥጥርና ክትትል ስራዎች በማጠናከር የኑሮ ውድነት ለመቀነስ እንደሚሰራ ተነስቷል።
በሌላ በኩል የአሰራር ስርዓትን በማዘመንና የዲጂታላዜሽን አሰራሮችን በማሳደግ እንዲሁም ተጠያቂነትን በማስፈን ሌብነትን የመከላከል፤ የሰላም እሴት ግንባታ ስራዎች የማሳደግ መንደርተኝነትን ለመቀነስ እንዲሁም ጠባቂነትና የጭቃ ቤትን የመቀነስ ስራ በትኩረት እንደሚሰራ ተመላክቷል።
ለአርሶ አደሩ ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ በክልሉ የሚታረስ መሬት ፆሙን እንዳያድር ለማድረግ በልዩ ትኩረት በመስራት በምግብ ራስን ለመቻልና ከተረጂነት ለመላቀቅ እንዲሁም ኮንትሮባንድ እና የመሬት ወረራና ህገወጥ ግንባታን ዜሮ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተጠቅሷል።
እንዲሁም የገጠር ኮሪደር የማፋጠን፣ የምርት ማከማቻ ግንባታን የማፋጠን፣ የምርት ማከማቻና የሽያጭ ማዕከልና አግሮ ፕሮሰሲንግ ግንባታ እንዲሁም የቱሪስት መዳረሻዎችን የማስፋት ስራም በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ ነው የተገለፀው።
የሌማት ትሩፋትን በማስፋት፣ የበጋ እርሻና የኩታ ገጠም ስራዎችን የማሳደግ እንዲሁም የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን የማሳደግ፤ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ተገቢው ድጋፍ በማድረግ እንዲጎለብት ማስቻል የማዕድን ዘርፉ ላይ ያሉ ሀብቶችን ለመጠቀም የሚሰሩ ስራዎች የማሳደግ ላይም በትኩረት እንደሚሰራ በውይይቱ ተጠቁሟል።
ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በማጠናከር ኢንዱስትሪዎችን የማሳደግ ስራ ላይም ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ተመላክቷል።