የመንግስት የፕሮጀክቶች የድጋፍና ክትትል ሥርዓት የመፈጸም አቅምን እያጎለበተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት የፕሮጀክቶች የድጋፍና ክትትል ሥርዓት የመፈጸም አቅምን እያጎለበተ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሣስ 8/2018 (ኢዜአ)፡-የመንግስት የፕሮጀክቶች የድጋፍና ክትትል ሥርዓት የመፈጸም አቅምን በጥራትና ፍጥነት በማስጠበቅ የዜጎችን ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚረዳ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ሀገራዊ የልማት ዕቅድ ክትትልና ግምገማ ፖሊሲ ግብዓት የማሰባሰብ የአውደ ጥናት መድረክ አካሂዷል።
በዚሁ ጊዜ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የመንግስት ኢንቨስትመንት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተገኔ ሃይሉ፤ የመንግስት የዕቅድ ክትትልና ግምገማ ሥርዓት በአፈፃጸም ላይ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ነው ብለዋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የክትትልና ግምገማ መመርያ ትግበራም የፕሮጀክት አስተዳደርና አመራር አቅምን እያጎለበተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በፕሮጀክቶች አፈፃጸም የተመዘገቡ ውጤቶችም መንግስት የፈጠረው የአሰራር ሥርዓት አቅም የልማት ክትትልና ግምገማ አቅም ስኬት መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ፖሊሲው ተዘጋጅቶ ከሁሉም ክልልና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር አውደ ጥናት ማካሄድ ማስፈለጉን አንስተዋል።
ሀገራዊ የልማት ዕቅድ ክትትልና ግምገማ ፖሊሲ ግብዓት የማሰባሰብ መድረኩም ወጥና የተናበበ የፕሮጀክት ግንባታ የዕቅድ ክትትል አቅምን ለማጎልበት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ይህም የፕሮጀክቶችን የመፈጸም አቅም በጥራትና ፍጥነት በማስጠበቅ የዜጎችን ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚረዳ አስረድተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፕላንና ልማት ቢሮ ሃላፊ ፍቃደስላሴ ቤዛ፤ ሀገራዊ የልማት ዕቅድ ክትትልና ግምገማ ፖሊሲው ሲተገበር የልማት አመራር ሥርዓት ውጤታማነትን ያስጠብቃል ብለዋል።
በተለይም በፌደራልና በክልል መንግስታት የዕቅድ አፈፃጸም ላይ የተናበበና ውጤታማ የአፈፃጸም ሥርዓትን ለመዘርጋት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል ፕላንና ልማት ኮሚሽን የኢኮኖሚ ልማት ዳይሬክተር አስፋው ወርቁ፤ የልማት ሥራዎችን በተናበበ የግምገማ ሥርዓት በመፈተሽ ስኬቶችንና ቀሪ ሥራዎችን ለመፈተሽ ይረዳል ብለዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕላንና ልማት ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሙባረክ አወል፤ ፖሊሲው በተቀናጀ የአመራርና አስተዳደር ውጤታማ የዕቅድ ክትትል ግምገማ ሥርዓትን መፍጠር ያስቻላል ብለዋል።