ቀጥታ፡

ተደራጅተን ተኪ ምርት ላይ በመሰማራት ውጤታማ ሆነናል - አምራች ማሕበራት

ዲላ፤ ታሕሳስ 8/2018 (ኢዜአ)፡- ከመንግስት ባገኙት ድጋፍ  ተደራጅተው ተኪ ምርት ላይ በመሰማራት  ውጤታማ መሆናቸውን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ የሚንቀሳቀሱ የጨረቃጨርቅና ሚስማር አምራች  ማሕበራት ገለጹ። 

በከተማው የተኪ ምርት አምራቾች ማሕበራትና ሌሎች የልማት የስራ እንቅስቃሴዎች  ዛሬ   በባለድርሻ አካላት የመስክ ምልከታ ተደርጓል።  


 

ከመንግስት ባገኙት ድጋፍ ተኪ ምርት   ላይ  ተሰማርተው በውጤታማነት በመቀጠለ ተጠቃሚ መሆናቸውን  አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ   አምራች ማሕበራት ገልጸዋል።

የ"ኖጲቾ ጋርመንት " ማሕበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ሞገስ እንዳሉት፤   በ2010 ዓ. ም በአነስተኛ ደረጃ  የጀመሩት የጨርቃ ጨርቅ ሥራ ውጤታማ በመሆን አሁን ላይ ወደ ባለሀብትነት ማደግ ችለዋል።


 

ከልማት ባንክ በሊዝ ፋይናንስንግ ያገኙት የ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የማሽነሪ ድጋፍ ስራቸውን ከማስፋት ባለፈ ካፒታላቸውን ከ25 ሺሕ ወደ 12 ሚሊዮን ብር ማደጉን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት እዳቸውን ከፍለው ለሁለተኛ ጊዜ በ10 ሚሊዮን ብር የሊዝ ፋይናንስግ የጨርቃጨርቅ ማተሚያ ማሽን ማስገባታቸውንም አንስተዋል።

ማሕበራቸው ከዚህ ቀደም    የሚያመርተውን በከፍተኛ   ደረጃ  ማሳደጉን ጠቅሰው፤ በዚህም ከውጭ የሚገቡትን የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች በሀገር ውስጥ እንዲተኩ በማገዝ   ተጠቃሚም እንደሆኑ  ተናግረዋል።

ከመንግስት ባገኙት የመስሪያና መሸጫ ቦታ የተለያዩ ይዘትና ዓይነት  ያላቸውን ሚስማር በማምረት ላይ እንደተሰማሩ  ያነሱት ደግሞ የሰለሞንና ስመኘው ሽርክና ማሕበር ሥራ እስኪያጅ አቶ ሰለሞን ተዋበ ናቸው።


 

በአሁኑ ወቅት ማሕበሩ በቀን ከ400 ካርቶን በላይ የሚስማር ምርት ለገበያ እያቀረበ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤  በዚህም የማሕበሩን ተጠቃሚነት  ከማረጋገጥ ባለፈ ለ12   ዜጎች ቋሚ የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።

የዲላ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ፣  የሥራና ክሕሎት መምሪያ ሃላፊ አቶ ታሪኩ ታደሰ፤  በከተማዋ ከሚገኙ 737 ማሕበራት መካከል 10 በተኪ ምርት ላይ የተሰማሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ከተሰማሩበት ውስጥ  የግንባታ ግብዓት፣ ጨርቃጨርቅና አልባሳት እንዲሁም የቢሮና ቤት እቃዎች ዘርፍ እንደሚገኙበት  ጠቅሰው፤  ባለፈው ዓመት ብቻ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ተኪ ምርት በከተማው መመረቱን አውስተዋል።

የጥሬ እቃ አቅርቦት ትስስርን በማጠናከርና የሊዝ ፈይናንሲንግ በማጠናከር ተኪ ምርት የሚያቀርቡ ማሕበራትን ቁጥር ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድር፣  የሥራና ክሕሎት ቢሮ ሃላፊ አበባየው ታደሰ(ዶ/ር)  በበኩላቸው፤  በክልሉ ዲላን ጨምሮ ተኪ ምርት ላይ የተሰማሩ ማሕበራት የአካባቢውን ገበያ ከማረጋጋት ባለፈ ከውጭ የሚመጣ ምርት ለማስቀረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ በተኪ ምርት ላይ  ለተሰማሩ ማሕበራት የተቀናጀ ድጋፍ በማድረግ አቅማቸውን በቀጣይነት የማጎልበቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

ኢንተርፕራይዞች የኢንዱስትሪ ልማት መሠረት መሆናቸውን ያነሱት ሃላፊው በቅርበት በመከታተልና በመደገፍ በተለይም ለስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ያላቸውን አቅም ማጎልበት  ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም