የወጣቶች ማእከላትን ለማዘመንና የሚሰጡትን አገልግሎት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የወጣቶች ማእከላትን ለማዘመንና የሚሰጡትን አገልግሎት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሣስ 8/2018 (ኢዜአ)፡- የወጣቶች ማእከላትን ለማዘመንና የሚሰጡትን አገልግሎት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር “የተገነባ የወጣቶች ስብዕና ሀገር ይገነባል” በሚል መሪ ሃሳብ ወጣቶች፣ የወጣት አደረጃጀቶች የኃይማኖት አባቶች የሀገር ሽማግሌዎችና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የተሳፉበት የፓናል ውይይት አካሂዷል።
በዚሁ ወቅት የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያግዝ የበለጸገ ወጣት ለማፍራት ፖሊሲዎችንና ፕሮግራሞችን በመቅረፅ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በጋራ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ በዚሁ ወቅት፤ በስብዕና የተገነቡ ወጣቶች ሀገር እንደሚገነቡ ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል ብለዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ የስብዕና መገንቢያ ማዕከላት ተገንብተው ለወጣቶች የእውቀት፣ የክህሎት፣ የስራ ፈጠራና የመዝናኛ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ማዕከላቱን ከማዘውተሪያነት ወደ ስብዕና ማበልጸጊያነት ለማሸጋገር የተለያዩ የንቅናቄ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የወጣቶች ስብዕና ግንባታ የቤተሰብ፣ የትምህርት ቤት፣ የሀይማኖት ተቋማትና የባለድርሻ አካላትን ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን ጠቁመው፤ በተደመረ አቅም ከሰራን ስብዕናው የተገነባ ትውልድ ማፍራት እንችላለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሀፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፤ አንዳንድ የሚስተዋሉ ከባህል ያፈነገጡ ድርጊቶችን፣ የስነ ምግባር ጉድለቶችንና ለሱስ ተጋላጭነት ለመቀነስ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት አለብን ብለዋል።
ጉባኤው በትውልድ ግንባታ ዙሪያ ከትምህርት ተቋማት፣ ከመገናኛ ብዙሃንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ ወጣቶች ለስብዕና ግንባታ ጠቃሚ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አተኩረን መስራት አለብን ብለዋል።
የሰላም አምባሳደር ወጣት ስለሺ ኡመር ወጣቶች ስብዕናቸውንና ሀገራቸውን በሚገባው ልክ በሚገነቡ ጉዳዮች እና ሀሳቦች ላይ መስራት አለብን ብሏል።
ወጣት ቅድስት በሀይሉ በበኩሏ በወጣቶች ስብዕና ግንባታ የቤተሰብ፣ ትምህርት ቤት እና የመገናኛ ብዙሃን አስተዋጽኦ ሊጠናከር እንደሚገባ ገልጻለች።
ወጣቶች ራሳችንን ለማብቃት በምናደርገው ጥረት የምንጠቀማቸውን የመረጃ ምንጮች መምረጥ አለብን ብላለች።