ቀጥታ፡

ሰላምን በዘላቂነት ለማፅናት ድጋፋችንን እናጠናክራለን - የጋዝጊብላ ወረዳ ነዋሪዎች

ሰቆጣ፤ ታህሳስ 8/2018(ኢዜአ)፡-የአካባቢያቸው ሰላም በዘላቂነት ፀንቶ እንዲቀጥል ከፀጥታ ሃይሉ ጎን በመሆን ሲያደርጉ የቆዩቱን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የጋዝጊብላ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ። 

ነዋሪዎቹ "ሁሌም ለሰላም ዘብ እንቆማለን" በሚል መሪ ሃሳብ  በሰላም ግንባታ ዙሪያ በጋዝጊብላ ወረዳ አስ ከተማ ዛሬ ተወያይተዋል። 


 

ውይይቱ  የተካሄደው  የመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖችና የብሔረሰብ አስተዳደሩ አመራሮች በተገኙበት ነው። 

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል  አቶ ተስፋዬ ወሰን፤ ቀደም ሲል ፅንፈኛው በአካባቢው ታዳጊ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ እንዲስተጓጎሉ በማደረግ ጭምር  በደል መፈፀሙን አስታውሰዋል። 

በአካባቢው ሕግ በማስከበር ሰላምን እንዲሰፍን በተከናወኑ ሥራዎች የበኩላቸውን ሲወጡ መቆየታቸውንና  በዚህም  ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል።


 

በቀጣይም የአካባቢያቸው ሰላም በዘላቂነት ፀንቶ እንዲቀጠል ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ነው የገለጹት።

ሌላው ተሳታፊ ወይዘሮ መሰሉ አታላይ ፤  "አጥፊዎችን በማጋለጥ ለሰላም ዘብ እንቆማለን " ብለዋል።

ችግሮች በውይይትና በሰላም እንዲቋጩ የሚደግፉ መሆኑን ገልጸው፤ በጫካ የቀሩ የመንግስትን ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ተቀብለው በመምጣት የበደሉትን ሕብረተሰብ እንዲክሱ የእናትነት ሚናቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በየደረጃው ያለው የፀጥታ ሃይል ለሕዝብ ሰላም መስፈን ሲባል ዋጋ እየከፈለ ነው፤ እኛም ከጎኑ በመሆን እያገዝን ነው  ያሉት ደግሞ  አቶ  አረጋ ሳሙኤል ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢያቸው የሰፈነውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል  በሚከናወኑ ሥራዎች እያደረጉት ያለውን እገዛ ይበልጥ እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።

የጽንፈኛውን እኩይ ተግባር ለመመከት ሕዝቡ አምርሮ በመታገል ሲያደርግ የቆየውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የተነገሩት ደግሞ በብልፅግና ፓርቲ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሰተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዳግም ባይነሳኝ ናቸው።

የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪና የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሹመት ጥላሁን ፤ የጋዝጊብላ ወረዳ  ሰላም ፀንቶ እንዲቀጥል የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ሌሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎች እገዛቸውን ይበልጥ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

የሰሜን ምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አሰፋ ቸኮል እንዳመለከቱት፤ ጽንፈኛው የታሪካዊ ጠላቶችን የጥፋት ተልዕኮ ለማስፈፀም ቢሞክርም በሕግ ማስከበር እርምጃ ማምከን ተችሏል።

መንግስት ያደረገውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደሰላም የመጡ እንዳሉ አንሰተው፤ የሰላምን አማራጭ በማይቀበሉት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። 

ሕብረተሰቡ ሰላምን ለማፅናት ሲያደርግ የቆየውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በውይይቱ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶችና ወጣቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም