ቀጥታ፡

ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ስለ ህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝት ምን አሉ?

የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገዋል። 

ሞዲ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሲያደርጉ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ከማንሞሃን ሲንግ በኋላ ኢትዮጵያን የጎበኙ ሁለተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ህንድ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ ጋር ያላትን የልማት አጋርነት ማሳደግን ያለመ ነው።

የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መክረዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በፓርላማ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። 

በአድዋ ድል መታሰቢያም የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።

ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ስለ ህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝት በስፋት ዘግበውታል። 

ዓለም አቀፍ የዜና ወኪሎቹ ሮይተርስ እና አሶሲዬትድ ፕሬስ ጉብኝቱን ከ"ጂኦ-ፖለቲካዊ" አንጻር ተመልክተውታል።

በተለይ ህንድ በኢትዮጵያ ያላትን የአምስት ቢሊዮን ኢንቨስትመንት አጉልተዋል።

አልጀዚራ ትኩረቱን ያደረገው ህንድ በ"ደቡባዊው ዓለም" (Global South) ላይ ያላትን ተጽዕኖ ለማሳደግ በምታደርገው ጥረት ላይ ነው። እንዲሁም የኢትዮጵያና የህንድ ስትራቴጂካዊ አጋርነት በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳም በስፋት አንስቷል። 

ቢቢሲ እና ፍራንስ 24 ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለየት ያለ አቀባበል ትልቅ የዲፕሎማሲያዊ መቀራረብ ምልክት መሆኑን ዘግበውታል።

የአፍሪካ ሚዲያዎች በበኩላቸው የናሬንድራ ሞዲን ጉብኝት "የአፍሪካ-ህንድ" ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ አድርገው ዘግበዋል። 

አፍሪካ ኒውስ እና ዘ ኢስት አፍሪካን ጉብኝቱ በአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ መደረጉን በማንሳት፣ ህንድ ከአህጉሪቱ ጋር ያላትን ወታደራዊ፣ የጤና እና የቴክኖሎጂ ትብብር እንደሚያጠናክረውም ገልጸዋል።

የደቡብ አፍሪካው ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ የናይጄሪያ እና ሌሎች የአፍሪካ መገናኛ ብዙሃን ህንድ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ኢትዮጵያን እንደ መግቢያ በር (Anchor) መጠቀሟን እና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሚኖረውን ተምሳሌትነት ዘግበዋል።

እንደ ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ (The Times of India) ፣ ኤንዲቲቪ (NDTV) እና ኤኤንአይ (ANI) ያሉ የህንድ መገናኛ ብዙሃን የሞዲን ጉብኝት ከፍተኛ ሽፋን ሰጥተውታል። 

የዘገባዎቹ ዋንኛ ትኩረት በኢትዮጵያ ፓርላማ ስላደረጉት ንግግር እና ስለተደረገላቸው ልዩ የክብር ሽልማት ነው።

በሌላ በኩልም የዲጂታልና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተደረጉ ስምምነቶችን በዝርዝር አቅርበዋል።

አጠቃላይ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ትኩረት ታሪክ፣ ስትራቴጂካዊ አጋርነት፣ የደቡብ ለደቡብ ትብብር ላይ ያጠነጠኑ ናቸው። 

የኢትዮጵያ እና ህንድ የሁለትዮሽ ትብብር ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ምዕራፍ መሸጋገሩንም በመገናኛ ብዙሃኑ በስፋት ተነስቷል። 

ኢትዮጵያ እና ህንድ የተባበሩት መንግስታ ድርጅት እና ብሪክስን ጨምሮ በሌሎች የባለብዙወገን መድረኮች ላይ የደቡባዊውን ዓለም ድምፅ ለማሰማት የጋራ ቁርጠኝነታቸውን መግለጻቸው በዘገባዎቹ በስፋት ተንጸባርቋል። 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም