የጋራ ትርክትን በመገንባት ሂደት ድጋፋችንን እናጠናክራለን - ኢዜአ አማርኛ
የጋራ ትርክትን በመገንባት ሂደት ድጋፋችንን እናጠናክራለን
ሆሳዕና ፤ ታህሳስ 8/2018(ኢዜአ)፦ መንግሥት የጋራ ትርክትን በመገንባት ሂደት እያደረገ ላለው ጥረት ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡
በከተማው የቦብቾ ቀበሌ ነዋሪው አቶ አለማየሁ ኤልያስ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ መንግሥት የጋራ ትርክትን በመገንባት ፈጣን ሀገራዊ እድገት ለማስመዝገብ እያደረገ ያለው ጥረት ይበል የሚያሰኝ በመሆኑ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
አሁን ላይ በመደመር መንግሥት ተግባራዊ እየተደረጉ የሚገኙ የልማት ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑን ጠቁመው የበለፀገች ሀገርን ለመገንባት አብሮነትን ከማጠናከር ባለፈ ሁሉም በተሰማራበት መስክ ጠንክሮ መስራት አለበት ነው ያሉት።
መንግሥት ሌብነትን የሚፀየፍ ትውልድ በመፍጠር ፈጣን እድገት እንዲረጋገጥ ትርጉም ያለው ስራ እየሰራ ይገኛል ያሉት ደግሞ በከተማው የሄጦ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ መሰረት አቢዮ ናቸው፡፡
እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎች የሚያስደስቱና የነገው ትውልድን ተስፋ የሚያለመልሙ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አበበ አያልቅበት በበኩላቸው፤የጎሰኝነትና ዘረኝነት አመለካከት በመውጣት በሀገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ አጠናክሮ ማስቀጠልና በተሰማራንበት የስራ መስክ በትጋት በመስራት ውጤታማነታችንን ማላቅ ይጠበቅብናል ብለዋል።