ቀጥታ፡

መሶብ የአንድ ማዕከል ፈጣንና የተሻለ አገልግሎት እንድናገኝ አስችሎናል - ተገልጋዮች

ሐረር፤ ታህሳስ 8/2018 (ኢዜአ)፡- መሶብ የአንድ ማዕከል ፈጣንና የተሻለ  አገልግሎት እንዲያገኙ ያስቻላቸው መሆኑን ተገልጋዮች ገለጹ።

በሀገር ደረጃ ከተነደፉ የተቋማት ማሻሻያ ፕሮግራሞች ውስጥ አንዱ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ነው።

ከዚህ ውስጥም የሐረሪ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪና የፌዴራል ፐብሊክ ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮምሽነር ወይዘሮ አልማዝ መሰለ  ህዳር 02 ቀን 2018 ዓ.ም ተመርቆ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ፤ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት  በፍጥነትና በዘመናዊ አሰራር እንዲገለገሉ ያስቻላቸው መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከተጠቃሚዎች መካከል አቶ ሙሉጌታ ታዬ፤ በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ ለመገልገል መምጣታቸውን ጠቁመው የመጡበትን ጉዳይ በ5 ደቂቃ መጨረሳቸውን  ተናግረዋል።

አገልግሎቱም ቀደም ሲል ይታይ የነበረውን እንግልትና የተወሳሰበ የአሰራር ችግር የፈታ በመሆኑ መደሰታቸውን ጠቁመው፤ እንዲህ ያሉ የዘመኑ አሰራሮች በሌሎችም መጠናከር እንዳለባቸው ተናግረዋል።


 

ቀደም ሲል አገልግሎት ለማግኘት ሰልፍ መጠበቅና እንግልት የሚስተዋልበት አሰራር ይታይ ነበር ያሉት ደግሞ አቶ ከሊፍ መሀመድ ናቸው። 


 

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማህበረሰቡ አገልግሎቶችን በፍጥነት እንዲያገኝ በማድረግ ጊዜንና ገንዘብን በመቆጠብ ረገድ እያበረከተልን  የሚገኘው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ደሊል ሙሳ በበኩላቸው፤ መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ እንግልትን ያስቀረ መሆኑን ጠቁመው በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ አገልግሎት እያገኘን ነው ብለዋል።



 

የአገልግሎቱ ወደ ስራ መግባት ከዚህ በፊት የነበረን ውጣ ውረድና ያልተገባ ወጪን ያስቀረ ስለመሆኑ  ጠቁመው  መንግስትም ይህን አሰራር በመዘርጋቱ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል።

የሐረሪ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ስራ አስኪያጅ አቶ አክራም መሀመድ  እንደገለጹት፤ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ ጊዜና ገንዘብ ቆጣቢ አሰራርን መሰረት ያደረገ ነው ። 


 

የማህበረሰቡን የአገልግሎት ጥያቄ በመመለስ ጥራትና ቅልጥፍናን በመጨመርና የብልሹ አሰራር ችግሮችን በማስቀረት የአገልግሎት እርካታን ማሳደግ እያስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል። 

የሐረሪ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ጆርዳን ይስሃቅ በበኩላቸው፤ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመጀመሪያው ዙር በሰባት ተቋማት ወደ 26  አገልግሎቶችን እየሰጠ  መሆኑን ተናግረዋል።


 

በሁለተኛው ዙር ደግሞ የመጀመሪያውን ጨምሮ 50 የሚደርሱ  አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ ጠቁመው ማዕከሉ የተገልጋይ መረጃ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን እያስቻለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም