ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ጥንታዊ ስልጣኔ እና ዘመናዊ ህልሞችን አጣምራ መያዟ ጸንታ እንድትቀጥል አድርጓታል 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 8/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ጥንታዊ ስልጣኔ እና ዘመናዊ ህልሞችን አጣምራ መያዟ በአይበገሬነት እና ጽናት መንፈስ እንድትቀጥል አድርጎታል ሲሉ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ገለጹ። 

የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን የጋራ ስብሰባ ላይ ንግግር አድርገዋል። 

የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ የሕግ አውጪ ምክር ቤት ፊት ንግግር በማድረጋቸው ትልቅ ክብር እንደሚሰማቸው ገልጸዋል። 


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ላበረከቱላቸው የኢትዮጵያ የክብር ኒሻን ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን የክብር ኒሻኑን በህንድ ህዝብ ስም ተቀብያለሁ ብለዋል። 

ኢትዮጵያ ከዓለም ጥንታዊ ስልጣኔዎች ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት እንደምትጠቀስም ተናግረዋል።

የሉሲ (ድንቅነሽ) ቅሪተ አካል ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኑን በግልጽ እንደሚያሳይ ነው የገለጹት። 


 

የኢትዮጵያ ታሪክ ህያው ሆኖ ዛሬም በመልክዓ ምድሯ እና የህዝቦቿ ልብ ላይ እንደሚታይ አመልክተው ኢትዮጵያ የጥንካሬ፣ የአይበገሬነት፣ የኩራት እና የለውጥ ምልክት ናት ብለዋል።  

ጥንታዊ ታሪክ እና ዘመናዊ ህልሞችን አጣምራ መያዟ የጥንካሬዋ ምንጭ መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የገለጹት። 

የመደመር ዕሳቤ የጋራ ትብብር ላይ ያተኮረ እና እሳቤው ህንድ ከምትጓዝበት መንገድ ጋር ተመሳሳይ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እና ህድን ጥንታዊ ስልጣኔ ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ገልጸው ነጋቸውን የተሻለ ለማድረግ በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም