የኢትዮጵያ እና ህንድ ትብብር ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት መሸጋገሩ የሀገራቱን ግንኙነት የበለጠ የሚያጸና ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና ህንድ ትብብር ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት መሸጋገሩ የሀገራቱን ግንኙነት የበለጠ የሚያጸና ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 8/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ እና ህንድ ትብብር ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት መሸጋገሩ የሀገራቱን ትስስር ማስፋትና ማጠናከር የሚያስችል እርምጃ መሆኑን የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ገለጹ።
የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን የጋራ ስብሰባ ላይ ንግግር አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህንድ እና ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ወዳጅነትና የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዳላቸው አንስተዋል።
የሀገራቱ የሁለትዮሽ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመረው ህንድ ከቅኝ ግዛት ነጻ በወጣችበት ማግስት እንደሆነም አውስተዋል።
ኢትዮጵያ እና ህንድ በባህል እና በትምህርት ያላቸው ትብብር የህዝብ ለህዝብ ቁርኝታቸው ይበልጥ እንዲጠብቅ ማድረጉን ነው የገለጹት።
የህንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ጠቅሰው ከአምስት ቢሊየን ዶላር በላይ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ በግብርና፣ ጨርቃጨርቅ እና ማኑፋክቸሪንግን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች መሰማራታቸውን አመልክተዋል።
ኩባንያዎቹ ከ75 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል መፍጠራቸውንም በንግግራቸው ጠቁመዋል።
ሀገራቱ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትብብራቸውን ማጠናከር የሚችሉባቸው በርካታ እድሎች እንዳሉም ነው ያነሱት።
ህንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ምዕራፍ ለማሸጋገር መወሰኗን ገልጸው ይህም ኢኮኖሚ፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቴክኖሎጂ፣ ማዕድን፣ አረንጓዴ ኢነርጂ እና ኢኖቬሽንን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።
የሁለቱን ህዝቦች በምግብ ዋስትና፣ በጤና እና አቅም ግንባታ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አንስተዋል።
ሁለቱ ሀገራት ግብርና፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች እርስ በእርስ በመማማር የጋራ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚቻል አመልክተዋል።
ህንድ ለኢትዮጵያ ዲጂታል ስትራቴጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ እድገት አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች ሲሉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ህንድን ታማኝ አጋር በማድረጓ አመስግነው ሀገራቸው የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር አበክራ እንደምትሰራ ተናግረዋል።