ቀጥታ፡

ፋይዳ መታወቂያ ለዲጂታል ኢትዮጵያ ስኬት ሚናው የላቀ ነው 

ሰመራ፤ ታህሳስ 8/2018(ኢዜአ)፦ ፋይዳ  መታወቂያ ለዜጎች ፈጣን አገልግሎትና ለዲጂታል ኢትዮጵያ ስኬት ሚናው የላቀ መሆኑን  የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዮዳሔ አርአያስላሴ ተናገሩ። 

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት ለአፋር ክልል ከፍተኛ አመራሮች በአገልግሎቱ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ዛሬ አካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮዳሔ አርአያስላሴ እንደተናገሩት፤  ፋይዳ መታወቂያ ለዲጂታል ስርዓት ግንባታ ያለው ሚና ወሳኝ ነው።

የዲጂታል ማንነት ሁሉም ቦታ ተደራሽ የመሆን፣ የዜጎችን ኑሮ የመቀየር እና አካታችነትን የማረጋገጥ ሰፊ አቅም እንዳለውም አመልክተዋል።

ወንጀልን ለመከላከልና ማጭበርበርን ለመቀነስ የሚያስችልና ለሀገር ደህንነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።

ለዜጎች ፈጣን አገልግሎትና ለዲጂታል ኢትዮጵያ ስኬት ሚናው የላቀ መሆኑን የገለጹት  ዋና ዳይሬክተሩ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ 90 ሚሊዮን ዜጎችን የመታወቂያው ባለቤት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አውስተዋል።

ለዚህም የሚያገለግሉ 7 ሺህ ማሽኖች አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም  የሕብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ የአመራሩ ሚና ከፍተኛ እንደሆነም አንስተዋል።


 

በብልፅግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ መሐመድ ሁሴን በበኩላቸው፤ መርሃ ግብሩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

ለመርሃ ግብሩ መሳካትና የዲጂታል ስራን ዕውን ለማድረግ አመራሩ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የአፋር ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም