በክልሉ ምርታማነትን በዘላቂነት ለመጨመር ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ተደራሽነትና አጠቃቀም ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ምርታማነትን በዘላቂነት ለመጨመር ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ተደራሽነትና አጠቃቀም ትኩረት ተሰጥቷል
አዳማ፤ ታህሳስ 8/2018(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ምርትና ምርታማነትን በዘላቂነት ለመጨመር የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተደራሽነትና አጠቃቀምን ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።
በኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ የአፈር ለምንት ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ እሸቱ ለገሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፤በክልሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት በተፈጥሮ ማዳበሪያ ላይ በተሰራው ስራ የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እየጨመረ መጥቷል።
በዚህ ዓመትም ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ መደበኛ፣ ቫርም ኮምፖስትና ከባዮ ጋዝ ተረፈ ምርቶች የተፈጥሮ ማዳበሪያ በስፋት እየተዘጋጀ ነው።
በአጠቃላይ በክልሉ 250 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ታቅዶ እስካሁን 105 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በክልሉ ከ300 በላይ የቨርም ኮምፖስት ማባዣ ማእከላት ተገንብተው የማባዛት ስራ እየተሰራ መሆኑን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ አርሶ አደሩም የተፈጥሮ ማደበሪያ ጥቅም እየተረዳ በመምጣቱ በስራው በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል ብለዋል።
በተያዘው ዓመትም ከተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ስራ ጎን ለጎን ተደራሽነትን ለመጨመር እና አጠቃቀምን ለማሻሻል በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።
ከተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀም አንጻርም ከክልሉ ግብርና ቢሮ ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ የግብርና ባለሙያዎች የአርሶ አደሩን ግንዛቤ ለማሳደግ እየተጉ መሆኑን አስረድተዋል።
በባሌ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት የአፈር ለምነት ቡድን መሪ ወይዘሮ ሮዛ ሙሐመድ በበኩላቸው፤ በዞኑ ምርታማነትን ለመጨመር በተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጃጀት ላይ ከአርሶ አደሩ ጋር በቅርበት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዞኑ 10 ወረዳዎች 13 የቨርሚ ኮምፖስት ማባዣ ማእከላት በመገንባት በእያንዳንዱ 60 ሳጥን ተዘጋጅቶ ኮምፖስት እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በእያንዳንዱ አርሶ አደር 18 ሜትሪኪዩብ መደበኛ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም 10 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ መደበኛ ኮምፖስት ዝግጅት በጥሩ አፈፃፀም ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
በተመሳሳይ የምዕራብ አርሲ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት የአፈር ለምነት ቡድን መሪ አብደላ ኢብራሂም፤ በዞኑ 14 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ መደበኛ ኮምፖስት ለማዘጋጀት ታቅዶ እስካሁን ከ13 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
በተለይም በዞኑ ቆላማ ወረዳዎች የኮምፖስት ዝግጅት ተቀናቆ ጥቅም ላይ ለማዋል በዝግጅት ላይ እንገኛለን ያሉት አቶ አብደላ በዞኑ በዚህ ወቅትም 150 ሺህ አርሶ አደሮች ቫርም ኮምፖስት እያዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል።