ቀጥታ፡

በጎንደር ለዘንድሮው የጥምቀት በዓል ከ2 ሚሊዮን በላይ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ ነው

ጎንደር ፤ ታህሳስ 8/2018(ኢዜአ)፦ በጎንደር ለዘንድሮው የጥምቀት በዓል "አንድ እንግዳ ለአንድ ቤተሰብ" በሚል መርህ ከ2 ሚሊዮን በላይ የውጭና የሀገር ውስጥ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ገለጹ።

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ በድምቀት ከሚከበርባቸው ከተሞች መካከል ጎንደር በግንባር ቀድምትነት የምትጠቀስ ሲሆን የበዓሉ አከባበር በታሪካዊነቱ፣ በባህላዊ እሴቱ እና በሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቱ ይታወቃል።

በዚህም መሰረት ለዘንድሮው የጥምቀት በዓል አከባበር እየተደረገ ያለውን ዝግጅት በተመለከተ ኢዜአ የከተማ አስተዳደሩን ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላን አነጋግሯል።


 

ምክትል ከንቲባዋ በማብራሪያቸው፤ የጥምቀት በዓል የጎንደርና አካባቢው ህዝብ እንግዶችን በመቀበል በደማቅ ስነ-ስርአት የሚያከብረው መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም መሰረት ለዘንድሮው የጥምቀት በዓል  ‘’አንድ እንግዳ ለአንድ ቤተሰብ’’ በሚል መርህ ከ2 ሚሊዮን በላይ የውጭና የሀገር ውስጥ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በጥምቀት በዓል ለመታደም የሚመጡ የሃገር ውስጥና የውጭ እንግዶችን በጥሩ መስተንግዶ በመቀበል እንዲያከብሩ በሁሉም ረገድ ዝግጅት ስለመደረጉ አንስተው ይህንኑ የሚከታተልና የሚያስፈፅም ኮሚቴ ተዋቅሮ ስራውን ጀምሯል ብለዋል።


 

በከተማው የሚገኙ ሆቴሎች የንግድና የህክምና ተቋማት እንዲሁም የትራንስፖርት ዘርፍ ማህበራት የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ዝግጁ ስለመሆናቸውም ተናግረዋል።

ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶች የ24 ሰዓት አገልግሎት የሚያገኙበትን አሰራር በመዘርጋትም ከዚህ ቀደም ተጥሎ የነበረውን የሰውና የተሽከርካሪ የምሽት እንቅስቃሴ ገደብ ከዚህ ወር ጀምሮ ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ መደረጉን ገልጸዋል፡፡


 

የቱሪስቶችን ቆይታ ለማራዘም እንዲቻልም ከበዓሉ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ የጎዳና ላይ የባህል ፌስቲቫል እንደሚዘጋጅ ጠቁመው ፌስቲቫሉ የጎንደርና አካባቢውን ባህል ወግና የእምነት እሴቶች ትዕይንት የሚቀርብበት ነው ብለዋል፡፡

በከተማው የተከናወኑ የኮሪደር ልማትና የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት እድሳት ቱሪዝሙን በማነቃቃት ለበዓሉ ልዩ ድምቀት የሚያጎናጽፍ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

የጥምቀት በዓል ዓለም አቀፍ ትኩረት ከተሰጣቸው የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ በመሆኑና የሁላችንም የጋራ ሃብት በመሆኑ ለስኬቱ ሁሉም የድርሻውን ለመወጣት መዘጋጀት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አለልኝ አይለው፤  ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶች የትራስፖርት እጥረት እንዳይገጥማቸው ከዚህ ቀደም የነበረውን 73 የስምሪት መስመር ወደ 83 የማሳደግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

የተጠናከረ የክትትልና የቁጥጥር የትራንስፖርት ስምሪት ስርዓት በመዘርጋት የመንገደኞችን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ መልኩ ለመጠበቅ የሚያስችል የተቀናጀ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም